ከሙስናጋር ተያይዞ መረጃ ለሚሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መብቶች ለማስጠበቅ መንግስት ቁርጠኛ ነው

158

ሠመራ (ኢዜአ) ጥር 5 ቀን 2015 ከሙስና ጋር ተያይዞ መረጃ ለሚሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢው የህግ ከለላና መብቶች ለማስጠበቅ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን የፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ አስታወቁ።

ምንጩ ያልታወቀ ሃብትን ለማጋለጥ የሃብት ምዝገባ ስርዓት ያለውን ፋይዳ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ ተካሄዷል። 

ኮሚሽነሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሀብት የማስመዝገብ ሂደት በመንግስት አሰራር ውስጥ የግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራር የማስፈን ዓላማ ያለው ነው።

ይህ አሰራር እውን መሆን የሚችለው በተወሰኑ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ጥረት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻዎች ንቁ ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ህብረተሰቡ ባለው ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር የሙሰኞችን የዕለት ተዕለት ተግባር በቅርበት የሚያይና ጠንቅቆም የሚውቅ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በሙስና የተዘፈቁ ወንጀለኞችን ለህግ በማጋለጥ ያለአግባብ የተመዘበሩ የህዝብ ሃብት ለማስመለስ ለተጀመረው ሀገራዊ የጸረ-ሙስና ትግል ስኬታማነት የማይተካ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በኮሚሽኑ የሃብት ምዝገባና ጥቅም ግጭት ማስወገድ ስራ ፈጻሚ አቶ መስፍን በላይነህ፤ በሀገሪቱ ከገቢ በላይ የሆነ ሃብት ማካበት በሙስና ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ገልጸዋል።

ይህንን ለመከላከል እንዲረዳ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ሃብትን የማስመዝገብ ስራዎች ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በኮሚሽኑ እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ሆኖም የተመዘበረ የህዝብ ሃብትን በማስመለስ ሂደት ከወንጀሉ ውስብስብነት ሌላ ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ ወንጀሉን ለመከላከል በቅንጅት የመስራት ባህል ያለመጎልበቱ እንቅፍት እንደሆነ አስረድተዋል።

የፍትህ አካላትና የፋይናንስ ተቋማት እየረቀቀ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመቆጣጠር የሚመጥን አሰራር ዘርግተው ህብረተሰቡን በማስተባበር ምንጩ ያልታወቀ ሃብትን ለማስመለስ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ኑር ጣሂር፤ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚስተዋሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ህብረተሰቡን እያስመረሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህ የእድገትና የብልጽግና ጸር የሆነው ችግር ከቃል ባለፈ በተግባር አምርሮ ለመታገል ካልቻልን የምንፈልገው ሀገራዊ ስኬት ላይ መድረስ አንችልም ብለዋል።

የክልሉ መንግስት በቅርቡ የጸረ-ሙስና ትግል ማቀጠል የሚያግዝ ኮሚቴ አደራጅቶ ወደ ስራ በገባበት ወቅት ይህ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በሠመራ መካሄዱ ትግሉን ለማሳካት መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥም በህብረተሰቡ ውስጥ የተሰገሰጉ ሙሰኞችን በማጋለጥ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በክልሉ የሃብት ምዝገባ ለመጀመር የህግ ማዕቀፎች በመዘጋጀታቸው በተያዘው ወር ወደ ስራ እንደሚገባ ያስታወቁት ደግሞ የአፋር ክልል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብዱ ሳልህ ናቸው።

ከዚህ አኳያ የምክክር መድረኩ በክልሉ መካሄዱ ለስራው ስኬታማነት ከላይ እስከታችኛው አመራር ወጥ የሆነ ግንዛቤ ለማስያዝ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በምክክር መድረኩ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም