ደኢህዴን 70 ከመቶ አመራሩን በአዳዲስ አመራሮች መተካቱን አስታወቀ

51
ሐዋሳ መስከረም 22/2011 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደኢህዴን)70 ከመቶ የሚሆነውን አመራሩን በአዲስ መልክ ማደራጀቱን የንቅናቄው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊው አቶ ሞገስ ባልቻ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ድርጅቱን እንዲመሩ ከተመረጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት 40ዎቹ አዳዲስ ናቸው። አመራሩም ሴቶች፣ ምሁራንና ወጣቶች አካቷል ብለዋል፡፡ በማዕከላዊ ኮሚቴ የተመረጡት ጠቅላላ  አባላትም 65 ናቸው፡፡ በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከተካተቱ 15 አባላት ውስጥም አምስቱ አዳዲስ አመራሮች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጉባዔው አመራሩን በአዲስ የማደራጀት ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ግልጸኝት በተሞላበት መንገድ አከናውኗል ብለዋል። በዚህም  ጉባዔተኛው  እያንዳንዱን ዕጩ ከመተቸት አንስቶ በምስጢር ድምፅ  አሰጣጥ  ድረስ በመጠቀም ምርጫውን ማካሄዱን አቶ ሞገስ አስረድተዋል። የድርጅቱን ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የደኢህዴንና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ  ዴሞክራሲዊነቱን ጠብቆ  መልኩ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ሂደቱ በአመራር መተካካት መርህ የተከናወነ ነው ያሉት አቶ ሞገስ፣ ከድርጅቱ ለተሰናበቱ ነባር አመራሮች የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡ ጉባዔው በቀረቡለት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት የተደረሰበት ውጤታማና ያስቀመጣቸውን ግቦችን ያሳካ እንደነበርም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የደኢህዴን 10ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የተደረገው ከመስከረም ከመስከረም18-22 /2011 ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም