ፍርድ ቤቱ አገልግሎት ፈላጊዎችን በተሻለ ለማስተናገድ የሚረዱ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

162

አዲስ አበባ ጥር 05/2015(ኢዜአ) የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አገልግሎት ፈላጊዎችን በተሻለ መልኩ ለማስተናገድ የሚረዱ የለውጥ ስራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በመገኘት የመስክ ምልከታ አካሂዷል።  

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በፍርድ ቤቱ ውስጥ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት፣ ወረፋ መጠበቂያ ስርዓት፣ ችሎት ማስቻያ ቦታዎችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ጎብኝተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከሰራተኞች፣ ዳኞችና የፍርድ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በድክመትና በጥንካሬ የተለዩ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።

በፍርድ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ፤ የዳኞች ቁጥርና መዝገብ አለመመጣጠን፣ የሰራተኞች ፍልሰትና የተቀላጠፈ አገልግሎት በሚፈለገው መልኩ አለመስጠት ከተነሱት ችግሮች መካከል ናቸው።

የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ እንደተናገሩት፤ ፍርድ ቤቱ ግልጽ ችሎት ማስቻል ላይ የበለጠ መስራት ይገባዋል።  

"በተለይም ዜጎች በፍጥነት ፍትህ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ብዙ ስራ ይጠበቃል" ያሉት ሰብሳቢዋ ይህን ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።  

ፍርድ ቤቱ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት ፖሊስንና ፍትህ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር አለበት ሲሉም አክለዋል።

ፍርድ ቤቱ ለሙስና በር ሊከፍቱ የሚችሉ አሰራሮችን ከማጥራትና የመፍትሄ እርምጃዎችን ከመውሰድ አኳያም የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ፍርድ ቤቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች የተሻሉ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ፉአድ ኪያር በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ በዓመት በአማካይ እስከ 145 ሺህ ድረስ መዝገቦችን እያስተናገደ ነው።  

ይህም ካለው የዳኛ ቁጥር አንጻር ትልቅ ጫና የሚፈጥር ቢሆንም ባለው አቅም ለማስተናገድ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።  

ዳኞች የሚሰጡት ውሳኔ ማስረጃ ላይ ብቻ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ሰፊ የለውጥ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ደንበኞችን ለማስተናገድ የተዘረጋው የአንድ መስኮት አገልግሎት ሌላው ውጤት እየተገኘበት መሆኑን አብራርተዋል።

ፍርድ ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት ማቋቋሙ ከተከናወኑ የለውጥ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም ገልጸዋል።  

"የጉዳዮች መዘግየትን ለማስቀረት 'የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ' በመተግበራችን ውጤት እያገኘን ነው" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አብንራርተዋል።    

በቀጣይም የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም