በኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ አንድነትን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል---የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

41
አክሱም መስከረም 22/2011 ኢህአዴግ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው በሃገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ውሳኔ ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁ አስተያየታቸውን የሰጡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። ዜጎች ህገ-መንግስቱና የፈዴራል ስርአቱን እንዲከበር የድርሻቸውን የሚያበረክቱበትን አቅጣጫም ጉባኤው ያስተላልፋል ብለው እንደሚጠብቁ ምሁራኑ ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የፖቲካል ሳይንስ መምህር ተክላይ ገብረመስቀል እንዳሉት፣ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ የሀገሪቱን እጣ ፈንታ የሚወስን እንደመሆኑ በወቅቱ በሀገራችን ውስጥ ያሉ ችግሮችን መንስኤና መፍትሄ በጥልቀት ማየት አለበት። ‘‘በሃገሪቱ ውስጥ የህግ ጥሰቶች በየቦታው ይታያሉ‘‘ ያሉት መምህሩ ችግሮቹን ለማስወገድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ከድርጅታዊ ጉባኤው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል። “ህዝቡ አብሮ መኖርና ማደግ መልማት ሲገባው እርስ በእርስ እንዲጠራጠር የማድረግ አባዜ ይታያል” ያሉት መምህር ተክላይ፣ጉባኤው ለዚህ ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ግንባታና ብሄራዊ መግባባትን ማጠናከር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን መወሰን አለበት” ብለዋል። “የሀገሪቱ ፖለቲካ የሚገኝበት ሁኔታና ኢህአዴግ እንደ ስርአት ያለበትን ቁመና በመፈተሽ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረውን የዴሞክራሲ  ምህዳርን የማስፋት ስራ አጀንዳ አድርገው በመወያየት የተጀመረውን ለውጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ይጠበቃሉ” ብለዋል። ሌላኛው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር አጽብሃ ተክለ በበኩላቸው ፣ ዛሬ ላይ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ዘርፎች በመላው ዓለም በርካታ ለውጦች እንዳሉ እየታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የህግ ጥሰትን ለማስቆምና በህዝቦች መካከል አንድነትና ብሄራዊ መግባባት እንዲጠናከር ኢህአዴግ በጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል። እህት ድርጅቶች የሚያጋጥሟቸው የአሰራር ጉድለቶች በጉባኤው መታየት እንዳለባቸው ጠቁመው ድርጅቶቹ ለክልላቸው ፣ ለግንባሩና ለሀገራዊ አንድነት የነበራቸውን አስተዋጽኦ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ጽጋቡ ሞትባይኖር እንደገለጹት  በሀገራችን አሁን ካሉ ችግሮች አኳያ ከኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ብዙ ውሳኔዎችን  ይጠበቃሉ። ከመገናኛ ብዙሃንና ኮሚዩኒኬሽን አደረጃጀት እና አሰራርም አንጻር ከጉባኤው ብዙ ውሳኔ እንደሚጠበቅ የገለጹት መምህሩ ኃላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ድረ-ገጾች አጠቃቀምና እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ይገመገማል ብለው እንደሚያስቡ አስረድተዋል። በሀገሪቱ የተስፋፋፉት መገናኛ ብዙሃን እንደ ትልቅ እድል ቢወሰዱም እስካሁን የታዩ ድክመቶችን በመለየት ለሀገራዊ ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ያላቸውን ቁመና ጉባኤው ሊፈትሽ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ‘‘ሚዲያዎች ፖለቲካው ወደ ሚነፍስበት መፍሰስ ሳይሆን ሙያውና ስነ-ምግባር በሚፈቅደው የህዝቡ ጀሮና አይን መሆን አለባቸው‘‘ ያሉት መምህሩ፣ ክፍተቶች ኢህአዴግ በመገምገም ጠንካራ ውሳኔ ያሳልፍበታል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ከመስከረም 23 እስከ25/2011 እንደሚካሔድ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም