የፈረንሳይና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የትግበራ ሂደት አደነቁ

142

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4 ቀን 2015 የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪ ኮሎናን እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባኤርቦክ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የትግበራ ሂደት አደነቁ።

የፈረንሳይ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውም እንዲሁ።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ማምሻውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የፈረንሳይና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመግለጫቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ችግር ለመፍታት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነትና የትግበራ ሂደት አድንቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን ጋር ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላት ገልፀው ይህ ጉብኝት ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር ተጨማሪ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በወቅታዊ፤ቀጠናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጎለብት ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት የምትሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ሰላም ዴሞክራሲ እና የልማት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም