በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ስም ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት በሚያጭበረብሩ ሰዎች ላይ እርምጃ እየተሰወሰደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ስም ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት በሚያጭበረብሩ ሰዎች ላይ እርምጃ እየተሰወሰደ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ስም ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት አባል ነን በማለት ኅብረተሰቡን እያጭበረበሩ በሚገኙ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት የደኅንነትና የሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አባል ነን የሚሉ ግለሰቦችን በተመለከተ በተለያዩ መንገዶች ክትትል ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በዚህ የማጭበርበሪያ ስልት የሚጠቀሙ አካላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል፡፡
ሰሞኑን በተደረጉ ጥብቅ ክትትሎችም
ፈለቀ ዴብሳ ደማ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02፤
አስፋው አዳማ ሙታ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01፤
ሳምሶን ገነነ መንገሻ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5፤
ተስፋ ሀተው ገምቴሳ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ሰበታ ክፍለ ከተማ፤
ዮሰን በቀለ ትክሳ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ክፍለ ከተማ
ሐሰተኛ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን መታወቂያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትንም ሐሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም ለሕገ-ወጥ ድርጊት የሚያውሉ ግለሰቦች በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ሥምሪት መያዛቸውን መረጃው ያመለክታል።
የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱንና የሌሎችን ተቋማት መታወቂያ አስመስለው በማሠራት የሚጠቀሙ ግለሰቦች መንግሥት የጀመረውን የጸረ ሙስና ትግል ተከትሎ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ጭምር ለማደናቀፍ ያለሙ መሆናቸውን መረጃው ጠቁሟል፡፡
ኅብረተሰቡ የመንግሥታዊ ተቋማት አባል ነን በማለት በሐሰተኛ መታወቂያ የማጭበርበር ድርጊት ለመፈጸም ከሚሞክሩ ግለሰቦች ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በ910 ነፃ የስልክ መስመርና Info@niss.gov.et በሚለው የኢሜይል አድራሻ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዲሁም በ816 እና 987 ነፃ የስልክ መስመር ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡