አዴፓ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ በቁርጠኛነት ይሰራል---አቶ ደመቀ መኮንን

76
ባህርዳር መስከረም 22/2011 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡ ዛሬን ጨምሮ ከመስከረም 17/2011 ጀምሮ ሲካሔድ የቆየው 12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ተጠናቋል። በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ሊቀመንበሩ እንደገለጹት የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስና ዜጎች ያለስጋት እንዲኖሩ ለማስቻል የህግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ  ነው። ወጣቱና መላው ህዝብ የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ ትግል የሚያደርግበት ወቅት መሆኑን ያስታወሱት ሊቀመንበሩ “ይህን የለውጥ ፍላጎት ተረድቶ መፍትሄ የሚሰጥ መሪ ሆኖ መገኘት ይገባል” ብለዋል። ለሁሉም ዜጎች መኖሪያነት እኩል የተመቸች አገር ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ተለይተው ያደሩ ችግሮችን በበሰለ የአመራር ጥበብ የመፍታቱ ጉዳይ ለነገ የማይባል የቤት ስራ መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረዋል። “እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታና ህዝቡ በነፃነት ተንቀሳቅሶ ሃብት ማፍራት እንዲችል አዴፓ የህግ የበላይነትን ማዕከል አድርጎ በቁርጠኝነት ይሰራልም” ብለዋል። አዲሱ የአዴፓ የለውጥ አመራር የአማራ ህዝብ ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች የተለየ ተጠቃሚ ተደርጎ የሚቆጠርበት የተሳሳተ ታሪክ በትክክለኛው ትርክት እንዲስተካከል በትጋትና በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አብራርተዋል። በህዝብ መስዋዕትነት የመጣውን ለውጥ ዳር ለማድረስ አዴፓ የክልሉን ህዝብ ሊጠቅም በሚችል መልኩ የፖለቲካ፣ የህግ ማሻሻያ፣ የአስተዳደርና የአሰራር ለውጦችን ፈትሾ እንዲስተካከሉም ያደርጋል ሲሉ አቶ ደመቀ አስታውቀዋል። ቀደም ሲል ከአጎራባች ክልሎችና ህዝቦች ጋር የተጀመረው የህዝብ ለህዝብም ሆነ ማንኛውም ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብት መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)  ላለፉት ስድስት ቀናት ባካሄደው 12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው 65 የማዕከላዊ ኮሚቴና 13 የስራ አስፈፃሚ አባላትን እንዲሁም የድርጅቱን ሊቀመነበርና ምክትል ሊቀ-መንበር ምርጫን አካሒዷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም