የደብረ ብርሃን የህግ ታራሚዎች በተመቻቸላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነናል አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የደብረ ብርሃን የህግ ታራሚዎች በተመቻቸላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነናል አሉ
86
ደብረ ብርሃን መስከረም 22/2011 የደብረ ብርሃን ማረሚያ ቤት የህግ ታራሚዎች በተመቻቸላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ ታራሚዎችን በሥነ ምግባር ከማነጽ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ አስታውቋል፡፡ ከታራሚዎቹ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተከሶ የሰባት ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደበት ቴዎድሮስ ሲሳይ ለኢዜአ አንደተናገረው በማረሚያ ቤቱ ያገኘውን ስልጠና ተጠቅሞ የወንዶች የውበት ሳሎን በመክፈት በወር ከ4 ሺህ 500 ብር በላይ ገቢ እያገኘ ነው፡፡ ስድስተኛ ዓመት የእስር ጊዜውን ያጠናቀቀው ቴዎድሮስ፣በገቢው ራሱንና ቤተሰቡን መጥቀም እንደቻለ አስረድቷል። የእርምት ጊዜውን ጨርሶ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀል የበደለውን ህዝብ በመካስ ለህግ የበላይነት መስፈን ድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡ ታራሚ ሚኪያስ ሞገስ በበኩሉ በማረሚያ ቤቱ በቂ የሙያ ሥልጠና ማግኘቱን ገልጿል፡፡ባገኘው የሙያ ስልጠና በመታገዝ የማረሚያ ቤቱን ካፍቴሪያ በወር 215 ሺህ በመከራየት በሚያገኘው ገቢ ራሴንና ስድስት ቤተሰቦቼን ለማስተዳደር ችያለሁ ብሏል፡፡ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተከሳ 16 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባት መስከረም መገርሳ በበኩሏ የሴቶች የውበት ሳሎን ስልጠና በመውሰድ በማረሚያ ቤቱ ሌሎች ሰልጣኞችን በማሰልጠን ገቢ እያገኘች መሆኗን አስታውቃለች፡፡ የሰሜን ሽዋ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኢንስፔክተር ዘውዱ ጌታቸው ታራሚዎችን በሥነ ምግባር ከማነጽ ጎን ለጎን ገቢ በሚያስገኙ ተግባራት መሰማራታቸውን ተናግረዋል። በዞኑ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙት ከሁለት ሺህ 500 በላይ የህግ ታራሚዎች በብረታ ብረትና እንጨት ሥራ፣ በእደ-ጥበብ፣ በህግ ማማከር፣ በትምህርት፣ በጸጉር ስራ፣ በምግብ ዝግጅትና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ሰልጥነዋል፡፡