በጉጂ ዞን ዘንድሮ በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ልማት ይካሄዳል

69
ነገሌ መስከረም 22/2011 በጉጂ ዞን በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ልማት እንደሚካሄድ የዞኑ ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ልማት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ በባለሥልጣኑ የቡና ልማት ባለሙያ አቶ አብዲሳ ለማ እንዳስረዱት በዞኑ ከሚያዝያ ጀምሮ የቡና ችግኞች ለመትከል የመሬት መረጣና ዝግጅት ከወዲሁ እየተደረገ ነው። በመንግሥትና በግል  በተዘጋጁ 1 ሺህ 605 ችግኝ ጣቢያዎችም 64 ሚሊዮን ምርጥ የቡና ችግኞችም ይተከላሉ።እስካሁን 96 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች ተፈልተዋል ብለዋል። ችግኞቹ ድርቅንና በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። በልማቱ 10 ሺህ 763 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሆነና የልማት ጣቢያ ሠራተኞችም የሙያ ድጋፍ  እያደረጉላቸው መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ባለሙያው ገለፃ በዞኑ አምና ከተተከሉት 52 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 78 ነጥብ 8 በመቶ ጸድቋል። በልማቱ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት መካከል በሻኪሶ ወረዳ ዲባ በቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኮንን ዱሎ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ ከሰብል ልማት በተጓዳኝ 5 ሺህ የቡና ችግኞች በግላቸው ለተከላ እያዘጋጁ ነው። እስካሁን በአንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ የቡና ልማት እያካሄድኩ ነው ያሉት አርሶ አደሩ፤ ከቡና የሚያገኙትን ምርት በመጨመር  ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ልማቱን እንደሚያስፋፉ ተናግረዋል። ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ አሪፍ ቡኖ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ዝናብ ለቡና ችግኝ ተስማሚ ስሆነ በዘንድሮ ልማት እስከ 10 ሺህ የቡና ችግኝ ለመትከል አቅጄ እየሰራሁ ነው ብለዋል። በተለይ ያረጀ የቡና ተክልን በመጎንደል በአዲስ ዝርያ ለመተካት ከባለሙያዎች ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በጉጂ ዞን 11 ወረዳዎች 105 ሺህ 640 ሄክታር መሬት በቡና ተክል ተሸፍኗል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም