ኩባ በአሜሪካ የተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲነሳላት ኢትዮጵያ በተመድ ድጋፍ እንድትሰጣት ጠየቀች

115
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 አሜሪካ ካለፉት ሀምሳ ዓመታት በላይ በኩባ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ  እንዲነሳ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንድትሰጣት ኩባ ጠየቀች። የአሜሪካ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ በኩባ ላይ የጣለውና 56ኛ ዓመቱን የደፈነው ማዕቀብ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብትና ዜጎች ህይወት ክፉኛ እየጎዳ መሆኑን በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል። የኩባ መንግስት የአገሪቱን ህገ-መንግስት ማሻሻልን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ እርምጃዎችን በመውሰድ ሁኔታዎችን ለመለወጥ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የአሜሪካ መንግስት ግን የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት የሚጎዱ እርምጃዎችን ማጠናከሩን ቀጥሏል ሲሉም አምባሳደሯ ገልፀዋል። በተለይም በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር መጠናከሩ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ ፈተና እያባባሰው ነው ሲሉም አምባሳደሯ  አመልክተዋል። ይህንን ጉዳት ማስቀረት ይቻል ዘንድም ኩባ በመጪው ጥቅምት መጨረሻ አሜሪካ ማዕቀቡን እንድታነሳ ለተባበሩት መንግስታቱ ድርጅት (ተመድ) ጥያቄ ለማቅረብ ማቀዷን አምባሳደር ቪልማ ቶማስ ጠቅሰዋል። በዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጎኗ እንዲሰለፍ አገራቸው እንደምትፈልግ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያም ከኩባ ጎን በመሰለፍ በተመድ መድረክ ላይ የድጋፍ ድምጽ ትሰጣት ዘንድ አምባሳደሯ የአገራቸውን መንግስት ወክለው ጠይቀዋል። ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በላይ በቆየው የአሜሪካ ማእቀብ ሳቢያ ብቻ ኩባ ከዓለም አቀፍ የወርቅ ገበያ ልታገኝ ትችለው የነበረውን ከ933 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ አጥታለች። ይህ ገቢ አሁን ባለው የዓለም ገበያ ሁኔታ ሲሳላ ደግሞ ከ134 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ውድቀት ያስከተለ መሆኑም ተመልክቷል። ኩባ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የምጣኔ ኃብት ውድቀት በማእቀቡ ሳቢያ ደርሶባታል። ከአሜሪካና እስራኤል በስተቀር ሁሉም የተመድ አባል አገሮች በኩባ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መነሳቱን ይደግፋሉ። ኢትዮጵያ እና ኩባ ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ ወዳጅነት አላቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም