''ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል'' -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

129

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት ከቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው ግንኙነት የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ስትራቴጂካዊ ትብብራዊ አጋርነት የተፈራረሙ መሆናቸውን ገልፀው ፤ይህን ስምምነት ይበልጥ ወደ ተግባር ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ምክክር ማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት እና ከፊል የዕደ ስረዛ ስምምነት መፈረሙ ተገልጿል።

ስምምነቱ የሁለቱን አገራት ጠንካራ ግንኙነትን ለማስቀጠል እና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋጋር እንደሚረዳ ተመላክቷል።

አቶ ደመቀ በውይይታቸው ለሚኒስትር ቺን ጋንግ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን እና ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልፀውላቸዋል።

የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በበኩላቸው ወዲዚህ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የመጀመሪያውን ጉብኝት በኢትዮጵያ በማድረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በሁኔታዎች ተለዋዋጭነት የማይዋዥቅ መሆኑን አስረድተዋል ።

ቺን ጋንግ "ዛሬ የተፈራረምነው የመግባቢያ ስምምነትም ይህን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው" ብለዋል።

በሁለትዮሽ ፣ቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ሚኒስትሮች ከውይይታቸው በኋላ የጋራ መግለጫ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም