ባንኩ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ 'ዳያስፖራ ሞርጌጅ ሴቪንግ አካውንት' የሚል የብድር አሰራር አዘጋጅቷል

68
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳያስፖራው በውጭ ያፈራውን ኃብት በአገር ልማት ላይ እንዲያውል የሚያስችለውን  'ዳያስፖራ ሞርጌጅ ሴቪንግ አካውንት' የተሰኘ አሰራር አዘጋጅቷል። ዳያስፖራው የብድር አሰራሩን በምን መልክ እንደሚጠቀምበትና በጋራ ለመስራት በሚያስችል ጉዳይ ላይ ከባንኩ ጋር መክሯል። በዚህም የተዘጋጀው የብድር አሰራር በዋናነት ለቤት መግዣና ለኢንቨስትመንት ማጠናቀቂያ/ፊኒሺንግ/ የሚውል እንደሆነም ባንኩ ገልጿል። በባንኩ የብድር አገልግሎት ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ እመቤት መለሰ አሰራሩን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። 'ዳያስፖራ ሞርጌጅ ሴቪንግ አካውንት' ያስፈለገበት ምክንያት የዳያስፖራው ማህበረሰብ በአገሪቱ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ ፍቃደኛ ቢሆንም የመኖሪያ ቤት እጦት እንደ ዋነኛ ተግዳሮት አድርጎ በተደጋጋሚ ማንሳቱን ተከትሎ ነው ብለዋል። ብድሩ ከመኖሪያ ቤት ባሻገርም ለተጀመሩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ማጠናቀቂያ የሚሆን የብድር አገልግሎትንም ያካተተ ነው ይላሉ። በዚህ አሰራርም የብድሩ ተጠቃሚ ለሚሆኑ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ብቻ ባንኩ ባመቻቸው የውጭ ምንዛሪ 'ዳያስፖራ ሞርጌጅ ሴቪንግ አካውንት'  መክፈት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ሂሳቡን ለመክፈትም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸውና የውጭ አገራት ነዋሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ፓስ ፖርት፣ የመኖሪያ ፍቃድና የስራ ፍቃድ የመሳሰሉትን ማሟላት እንደሚገባቸው በማብራሪያቸው ጠቁመዋል ዳይሬክተሯ። በተከፈተው ሒሳብ ላይ 20 በመቶውን ተቀማጭ ማድረግ የፈለገ ዳያስፖራ 80 በመቶውን ባንኩ በብድር ሸፍኖለት የቤት ግንባታውንም ሆነ ግዥውን መፈጸም እንደሚችል በመግለጽ ብድሩንም በ20 ዓመት እንዲከፍል ይደረጋል። ይህም ደግሞ ዳያስፖራው የሚከፍለው የወለድ መጠን በየዓመቱ 10 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚሆንም ወይዘሮ እመቤት ገልጸዋል። በተጨማሪም 30 በመቶ ሒሳብ ላይ ተቀማጭ የሚያደርግ ዳያስፖራም እንዲሁ ለ20 ዓመት የሚቆይ የ70 በመቶ ብድር ባንኩ የሚሸፍንና የወለድ መጠኑ በየዓመቱ 9 ነጥብ 5 በመቶ ይሆናልም ብለዋል። 40 በመቶ ተቀማጭ ማድረግ ለሚፈልጉ ዳያስፖራዎችም እንዲሁ ለ20 ዓመት የሚቆይ የ60 በመቶ ብድር እንደሚሰጠው አክለዋል። ለዚህም ደግሞ በየዓመቱ 8 ነጥብ 5 በመቶ ወለድ መክፈል ይጠበቅበታል። ዳያስፖራው 50 በመቶውን መክፈል የሚችል ከሆነ ደግሞ 50 በመቶ የሚሆነውን ብድር ባንኩ 20 ዓመት በሚቆይ ክፍያ የሚያበድር እንደሆነና በ8 ነጥብ 5 በመቶ ወለድ ብድር ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ባሉበት ሀገር ሆነው የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብድር አሰራሩ መካተት እንደሚችሉም አንስተዋል። የውይይቱ ተሳታፊ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው ባንኩ የብድር አሰራሩን ከማመቻቸቱ በፊት ሌሎች ተቋማትን ጨምሮ ከዳያስፖራ አባላት ዙሪያ ውይይት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። የመሬት ጉዳይ፣ የህግ የበላይነት፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ ፋይናንስ ፣ የጥቁር ገበያ ቁጥጥር እንዲሁም የዋስትና ጥያቄዎች በቅድሚያ ሊፈቱ ከሚገቧቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው እንደ ዳያስፖራዎቹ ገለጻ። ተሳታፊዎቹ ላነሱት ጥያቄም የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም ዳያስፖራዎቹ ያነሱት ጥያቄ መሰረታዊ መሆኑን በመጠቆም ባንኩ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ብቻ እንደሚመለከት ገልጸዋል። በተጨማሪም ዳያስፖራው  በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በስራና በትምህርት ያዳበሩትን ልምድ ለአገሪቱ የሚያውሉበት ወቅት አሁን በመሆኑ የተፈጠረውን አጋጣሚ እንደ መልካም እድል በመቁጠር አገሩን ለማልማት ቁርጠኛ መሆን ይገባዋል ብለዋል። አገሪቱ ካላት የገንዘብ ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመኖሩ ዳያስፖራው ይህንን ከግምት በማስገባት የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፣ ሙሉ በሙሉ የተመቻቸ ሁኔታን እንዳይጠብቁ በማውሳት። ይሁን እንጂ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ተቋማት ተግባብተው በመስራት ላይ ክፍተቶች እንዳሉባቸው በመግለጽ ዳያስፖራው ችግሩን ተረድቶና ተቋቁሞ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በዜጎች እኩልነትና የዴሞክራሲ ምህዳር የሰፋባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሁሉም ዘንድ መነሳሳት ተፈጥረዋል ያሉት አቶ ባጫ፤  በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ዳያስፖራው ለአገሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባልም ብለዋል። በተለይም ባንኩ ባመቻቸው የብድር አሰራር ተሳታፊ በመሆንና ልማቱን በማፋጠን የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ በመግለጽ። በዚህም ደግሞ ባንኩ ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና በተለያዩ አገራት ቅርንጫፎች ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው፤ ይህም ለዳያስፖራው ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም