በማሌ ወረዳ በ67 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ የተገነባው የሌሞ ጌንቶ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተመረቀ

255

ጂንካ ጥር 01 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ወረዳ 67 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባው የሌሞ ጌንቶ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተመረቀ።

የአካባቢው ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ የነበረው በደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ ወረዳ የሌሞ-ጌንቶ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኦሞ ሹሊ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሌሞ-ጌንቶ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ህንፃ ግንባታ ለማጠናቀቅ 66 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል።

ግንባታው ሰኔ 2009 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በመጓተቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የዞኑ አስተዳደር የማህበረሰቡን ቅሬታ በመቀበል ቀደም ሲል ከወሰደው የህንፃ ተቋራጭ ጋር የተገባውን ውል በመሰረዝ በሚያዝያ 2014 ዓ.ም ከሌላ ተቋራጭ ጋር በድጋሚ ውል መግባቱን ጠቁመዋል።

ለህንፃ ግንባታው በተሰጠው ትኩረትም አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸው፤ በዚህም ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑንም አቶ ኦሞ ሹሊ አስታውቀዋል።

የሌሞ-ጌንቶ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ ባህሩ ሙላት በበኩላቸው፤ ኮሌጁ የ2014ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ከተገለፀበት ቀን ጀምሮ በአጫጭር የስልጠና መስኮች የመማር ማስተማር ስራውን እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

የመማር ማስተማር ስራውን መጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀው፤ የሰው ሃይልና የመማሪያ ቁሳቁስ ከሟሟላት ጀምሮ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ እንደሆነም አስታውቀዋል።

በ66 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የተገነቡት የኮሌጁ ህንፃዎች የአስተዳደር ህንፃን ጨምሮ 3 የዎርክ ሾፕ ብሎኮች፣ 5 የመማሪያ ክፍሎች እና አንድ ቤተ-መፃሕፍትን ያካተቱ ናቸው ።

በህንጻው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ፤ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር እንዳልካቸው ጌታቸውና የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም