በጤና ተቋማት የተጀመረው ወቅታዊ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች ምዝገባ ሂደት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገበበት ነው

256

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 በጤና ተቋማት የተጀመረው ወቅታዊ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች ምዝገባ ሂደት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገበበት መሆኑን የአዲስ አበባ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው በ2014 በጀት ዓመት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና ከመንግሥታቱ ድርጅት የሕጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር ሰፊ የውልደት መጠን በሚከሰትባቸውና በተመረጡ 33 ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በቋሚነት የልደትና የሞት ምዝገባ ሥርዓት ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወሳል።  

ይህንንም ተከትሎ በዛሬው ዕለትም በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የሚከሰቱ የልደትና ሞት ምዝገባ ሥራዎች ያሉበት ደረጃ ተገምግሟል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ በጽህፈት ቤት ደረጃ ብቻ ሲሰጥ መቆየቱ ጠቅሰው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚገኙ አምስት የጤና ተቋማት የተጀመረው አገልግሎት አሁን ላይ ወደ 33 የጤና ተቋማት ማደጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በተቋማቱ የሞትና የልደት ኩነትን የሚመዘግብ የክብር መዝገብ ሹም ባለሙያ መኖሩም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥራዎቹን እያቀላጠፈው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ኅብረተሰቡ አገልግሎቱን ባገኘበት ጤና ተቋም እንዲያገኝ ማስቻሉን ነው የገለጹት።  

አሁን በተዘረጋው አሰራርም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ12 ሺህ በላይ ሕጻናት ከህክምና ተቋማት የልደት የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

እንደ አገር ለኅብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት ለማቅረብ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አስፈላጊ በመሆኑ እያንዳንዱ ግለሰብ እነዚህን ክስተቶች በወቅቱ በማስመዝገብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሙሉጌታ እንዳለ በበኩላቸው በጤና ተቋማት እየተሰጠ ያለው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መሻሻሎች እየታዩበት መሆኑን አንስተዋል።

አገልግሎቱ መሰጠት በጀመረበት ወቅትም የግንዛቤ እጥረት እንዲሁም ባለሙያዎች የሚሰሩበት ቢሮ እጥረት እንደነበር አንስተዋል።

በዘንድሮው ዓመት ኤጀንሲው ከመዘገባቸው ወቅታዊ ወሳኝ ኩነቶች አብዛኞቹ ከጤና ተቋማት የተወሰዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በጤና ተቋማቱ እየተሰጠ ያለው የምዝገባ አገልግሎት አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣይም አገልግሎቱን የማስፋትና የማዘመን ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸው በተለይም የቢሮ እጥረቱን ችግር ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም