ስነ-ምግባር የተላበሰ ትውልድ በመፍጠር የአገር ግንባታውን ለማገዝ እየሰራ መሆኑን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ገለጸ

114

ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 ስነ-ምግባር የተላበሰና በግብረ ገብነት የታነጸ ትውልድ በመፍጠር የተጀመረውን የሃገር ግንባታ ስራ ዳር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር “ትምህርታዊ ግብረ ገብነት ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የትምህርት ጉባኤ አካሄዷል።

ፕሬዝዳንቱ በጉባኤው ላይ እንዳሉት የሃገር ግንባታና የህዝብ መለወጥ የሚሳካው በእውቀትና ክህሎት የዳበረ እንዲሁም ስነ-ምግባር የተላበሰ ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው።

በሀገሪቷ በትምህርት ተደራሽነትን በማስፋትና በግብአት አቅርቦት ረገድ የተሻለ ጥረት ቢደረግም የተማሪዎች ስነ-ምግባርና ግብረ ገብነት እየተጓደለ በመምጣቱ ለቀጣይ ትልቅ ስጋት መፈጠሩን ገልጸዋል።

በየደረጃው ያለው የትምህርት አመራር፣ ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በመተባበር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባህርዳር ዩኒቨርሲቲም በእውቀት ላይ የተመሰረተ ችግርን የመፍታት ተቋማዊ አቅም በመገንባት በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

''በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በስልጠና፣ በቁሳቁስና ሌሎች መንገዶች እየደገፍን ነው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው ናቸው።

አሁን በከተማዋ በአንድ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጀመረው በስፖርት፣ ጤናና ትምህርት ማሻሻል ፕሮጀክት ወደ 22 ትምህርት ቤቶች በማሳደግ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ይህም የትውልድ ግንባታውን በትምህርትና እውቀት የታገዘ በማድረግ ለአገራችን እድገት መሰረት የሆነ የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሃይለማርያም እሸቴ በበኩላቸው በከተማዋ በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እስካሁን ውጥነት ያለው ስራ በትምህርት ዘርፉ ላይ ባለመሰራቱ የትምህርት ጥራቱ ላይ ችግር እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ያለውን እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ከቅድመ መደበኛ ደረጃ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች ስነ-ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።

በጉባኤው ላይ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲሁም ስነ-ምግባርና ግብረ ገብነት ላይ ያተኮሩ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል።

በጉባኤው ላይም በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራኖች፣ መምህራን፣ የወላጅ ኮሚቴ፣ ተማሪዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም