በሰሜን ሸዋ ዞን የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በበጋ ወቅት ለማስቀጠል እየተሰራ ነው

81
ደብረ ብርሃን መስከረም 22/2011 በክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ የተገኙ ስኬቶችን በመገምገም በበጋ ወራት ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ። በዞኑ በክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሳተፉ 430ሺህ 782 ወጣቶች 708 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ በጉልበት፣ በዕውቀትና በቁሳቁስ አድርገዋል። በመምሪያው የወጣቶች ጉዳይ ማካተትና ተሳትፎ ንቅናቄ ቡድን መሪ ወይዘሮ እመቤት ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ወጣቶቹ የሕዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ለ25 ቀናት ባደረጉት እንቅስቃሴ ለ101 ሰዓት አገልግሎት  ተሰጥቷል። ወጣቶቹ 277 የእቅመ ደካማ ቤቶችን ጠግነዋል።31 መኖሪያ ቤቶችም ገንብተዋል። እንዲሁም 20ሚሊዮን ችግኞች በመትከል፣ 4ሺህ 326 ሄክታር መሬት በመሥመር በመዝራትና ከ150ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ጥቁር አፈር በማጠንፈፍ ለምርትና ምርታማነት ማደግ እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከ11ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠታቸውን ወይዘሮ  እመቤት አስታውቀዋል። በጤናው ዘርፍም 805 ዩኒት ደም በመለገስ፣ ለኅብረተሰቡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን  ለመከላከያ ትምህርት ሰጥተዋል። በዘርፉ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ደግሞ በጤና ተቋማት ተመድበው ሙያዊ አገልግሎት መስጠታቸውን አስረድተዋል። የአገልግሎት አሰጣጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥም ስኬቶችን በመገምገምና ክፍተቶችን በመለየት በበጋ ወቅት 261ሺህ በላይ ወጣቶችን በአገልግሎቱ ለማሳተፍ መታቀዱን የቡድን መሪዋ አስታውቀዋል። በደብረብርሃን ከተማ በንግድ ስራ የሚተዳደረው ወጣት ደመቀ ሐብቴ በሰጠው አስተያየት 27ሺህ ብር ለበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ በመስጠት ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ አንዲት ግለሰብ ቤት እንዲገነባላቸው አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጿል። በአገልግሎቱ  በመሳተፍ ተንከባካቢ የሌላቸዉን አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ በላይ የሚያስደስት ነገር የለም ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል። የቀበሌ 03 ነዋሪ ወጣት ቢኒያም ገረመው በበኩሉ በክረምት ወራት በደም ልገሳና በከተማ ንጽህና ተግባር ተሳትፌያለሁ ብሏል። ከጓደኞቹ ጋር ሆኖም ማህበረሰቡን በማስተባበር በሚያገኙት ገንዘብ ከተለምዶ ማዕከል ከሚባለው ሥፍራ እስከ አሥመራ በር ያለውን የመኪና መንገድና የእግረኛ መንገዶችን ቀለም በመቀባት የትራፊክ አደጋን በመከላከልና የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ መስራታቸውን ገልጿል። በክረምቱ የጀመሩትን አገልግሎት ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር በበጋ ወራት በማስቀጠልም ለከተማዋ ዕድገትና ለነዋሪዎቹ ተጠቃሚነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብቷል። በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች  የተሰራላቸው ቤት ተስፋ እንዲሰንቁ ና   ወገን እንዳቻላቸው የተረዱበት እንደሆነ የተናገሩት በከተማዋ የቀበሌ 03 ነዋሪ የሆነችው ወይዘሮ ገነት መሐመድ ናቸው። የከተማ ወጣቶች ገንዘብ በማሰባሰብ፣ በዕውቀታቸዉና በጉልበታቸው ላበረከቱላት አስተዋጽኦ ምስጋናም አቅርበዋል። ለአንድ ወር ያህል በተካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም