ዳያስፖራው በስራና በትምህርት በውጭ አገራት ያዳበረውን ልምድ ለአገሪቱ ሊያውል ይገባል-አቶ ባጫ ጊና

104
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 ዳያስፖራው በውጭ አገራት ያዳበረውን ዕውቀትና ልምድ ለአገሩ የሚያውልበት ወቅት አሁን በመሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ተሳትፎውን ሊያጎለብት እንደሚገባ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ዳያስፖራው ማህበረሰብ በጋራ ሊሰሩባቸው በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት እያካሄዱ ነው። የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በስራና በትምህርት ያዳበሩትን ልምድ ለአገሪቱ የሚያውሉበት ወቅት አሁን ነው። በተጨማሪም የዜጎች እኩልነትና የዴሞክራሲ ምህዳር የሰፋባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሁሉም ዘንድ መነሳሳት ተፈጥረዋል ያሉት አቶ ባጫ፤  በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም ዳያስፖራው ለአገሩ የበኩሉን አስተዋፅጾ እንዲያበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል። በዚህም ደግሞ ባንኩ ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና በተለያዩ አገራት ቅርንጫፎች ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው፤ ይህም ለዳያስፖራው ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ብለዋል። ለውጭ ምንዛሬ የሚከፈት የባንክ ሂሳብ እንዲኖር ለማድርግም እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም። በውይይቱ የባንኩ የቢዝነስ ዴቭሎፕመንት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ይስሃቅ መንገሻ የባንኩን ታሪካዊ ዳራና አሁን ያለበትን በሚመለከት የውይይት ጽሁፍ አቅርበዋል። የባንኩ የብድር አገልግሎት ዘርፍ ወይዘሮ እመቤት መለሰም እንዲሁ ስለ ባንኩ የብድር አገልግሎት አሰራሮች ላይ ገለጻ ያደርጋሉ። በመጨረሻም የውይይቱ ታዳሚ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሳት ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።                                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም