ሕብረተሰቡ ለበዓል ወቅት የሚሸምተውን ምግቦች የመጠቀሚያ ጊዜና ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ ይገባዋል

169

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ታህሳስ 26/2015 በመጪዎቹ በዓላት ሕብረተሰቡ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦችን ሲገበያይ የመጠቀሚያ ጊዜያቸውንና ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በበዓል ወቅት በርካታ ምግብና መጠጦች ለገበያ  ይቀርባሉ፤ ሕብረተሰቡም  በብዛት ይሸምታል።

ይህንን የግብይት ወቅት ተገን በማድረግ ሕገ-ወጦች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ወደ ገበያ በማቅረብ ሕብረተሰቡን ለጉዳት ይዳርጋሉ።  

በባለሥልጣኑ  የምግብ ደኅንነት ኢንስፔክተር መሀመድ ሁሴን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሕብረተሰቡ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦችን የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን እያስተዋለ መግዛት አለበት፡፡

በተለይ መጪዎቹን የበዓል ወቅቶችን አስታኮ በርካታ ጊዜያቸው ያለፋባቸው ምግቦችና መጠጦች በቅናሽ ዋጋ ወደ ገበያ ሊወጡ ስለሚችሉ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ከምግብ ጋር  የተለያዩ ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል አላስፈላጊ ትርፍ ለማጋበስ ከሚጥሩ ሕገ-ወጦች ራሱን እንዲጠብቅ መክረዋል።

ሕብረተሰቡ የሚገዛቸውን የምግብና የመጠጥ ምርቶች በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ምርቶቹን ከመግዛቱ በፊት ማን እንዳመረታቸው? መቼ እንደተመረቱና? የመጠቀሚያ ጊዜያቸው መቼ እንደሚያልቅ? በአግባቡ ማየት አለበት።

ከእነዚህ ምግቦችና መጠጦች መካከል ጁሶች፣ የተለያዩ የታሸጉ ብስኩቶችና ሌሎች መጠጦች ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በተለይ ሕገ-ወጥ የሆኑና ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ወይም በክልል ጤና ቢሮዎች ሥር ባሉ ተቆጣጣሪ የፈቃድ ማረጋገጫ ሳይወስዱ የምግብ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሕገ-ወጦች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የራሱን መቆጣጠሪያ ስልቶችን ነድፎ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡ ለዚህ ሥራ የሚሰጠው መረጃ ቀላል ባለመሆኑ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

"ሕገ-ወጦችን የመከላከል ሥራ ለባለሥልጣኑ እና ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚተው አይደለም" ያሉት አቶ መሀመድ ሕብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት ተግባራትን በሚያስተውልበት ጊዜ ለባለሥልጣኑም ሆነ ለተቆጣጣሪ አካላት በመጠቆም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በተያዘው ዓመት በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ሰባት ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም