ብዝሀነትን ለልማትና ዕድገት ለማዋል እንሰራለን

151

ሚዛን አማን (ኢዜአ) ታኅሳስ 26 ቀን 2015 ብዝሀነትን ጠብቀን ለልማትና ለእድገት ለማዋል እንሰራለን ሲሉ የደቡብ የምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ አስታወቁ ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 70 አባላትን ያካተተ  የብሔረሰቦች ምክር ቤት ትላንት ተመስርቷል  ።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሆነው የተመረጡት አቶ መቱ አኩ ለኢዜአ እንዳሉት በተፈጥሮ የተቸርናቸው ብዝሃነቶች ውብና ልዩ ሀብቶቻችን በመሆናቸው ለልማት ለማዋል እንሰራለን።

ክልሉ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩል የመልማት ፍላጎት በማዳመጥ ፍትሃዊነትን ለማስፈን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ መተባበር አለባቸው" ያሉት አፈ ጉባኤው ብዝሃነትን ለልማትና ዕድገት ኃይል ማድረግን መሠረት ያደረገ ተግባር እንደሚከናወን አመላክተዋል ።

አንዱ ለአንዱ አቅም በመሆን በመደመር እሳቤ ለዕድገትና ለለውጥ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት እንደሚገባ ጠቁመው  ለተግባራዊነቱ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር ምክር ቤቱ እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

ትላንት በህዝብ ውስጥ የተዘሩ የተዛቡ ትርክቶችና ዜጎችን ለእንግልት የሚዳርጉ ጥላቻና መገፋፋትን በመተው "የኢትዮጵያን መጻኢ የሰላምና የብልጽግና ተስፋ እውን የሚያደርጉ ተግባራትን ለመፈጸም እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

መደጋገፍና አብሮነት በህዝብ ውስጥ ከጎለበተ የኢትዮጵያ ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ ይሸጋገራል ያሉት አፌ ጉባኤው ለተግባራዊነቱ ህዝቡ ከምክር ቤቱ ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን እንዲወጣ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለሀገር ትልቅ ተስፋ መሆኑን ጠቁመው "ከብሔረሰቦች መልካም ባህልና የሰላም እሴቶች ጋር አጣምሮ በማልማት ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ጥረት ይደረጋል" ብለዋል።

በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች እኩል ተጠቃሚ ሆነው በብልጽግና ጉዞ ላይ የጋራ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በአብሮነት ትስስር ውስጥ የጋራ ልማትና ዕድገት ለማምጣት የብሔረሰቦች ምክር ቤት የተቋቋመበትን ህገ መንግስታዊ መሠረት ሳይለቅ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል።

"የብሔረሰቦች ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ወግ ሳይበረዝ እንዲያድግ የብሔረሰቦች ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበትና በቅንጅት ይሰራል" ብለዋል።

ምክር ቤቱ የክልሉን የበጀት ቀመር የማዘጋጀትና የመወሰን ኃላፊነት እንዳለው ጠቅሰው የክልሉ ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የማቋቋም ሥራ በቀጣይ እንደሚሰራ አፈ ጉባኤው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም