“ከካኩማ እስከ ኳታር”

324

(በይስሐቅ ቀለመወርቅ)

አወር ማቢል 27 ዓመት ሞልቶታል ፡፡ በካታር የዓለም ዋንጫ ታሪክ ከሰሩ ተጫዋቾች አንዱ ነው ፡፡ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ  ተጫውቷል።ያለፈበት መንገድ ግን ለብዙ ወጣቶች አርዓያ የሚሆን ነው ፡፡

ለየትኛውም ተጫዋች ቢሆን የዓለም ዋንጫ የተለየ ስሜት ይፈጥራል ፡፡ ለማቢል የአስገራሚ የሕይወት ጉዞው አስደሳች መጨረሻ ሆነ ፡፡ የሕይወት ዘመኑን የመጀመሪያ አስርት ዓመታት በስደተኛ ካምፕ ላሳለፈ ሰው አጋጣሚው ይለያል ፡፡

የማቢል ወላጆች ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው ፡፡ በ1994 በጦርነት የምትታመሰዋን የቀድሞ የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ለቅቀው ወደ ካኩማ አመሩ ፡፡ ካኩማ በኬንያ የሚገኝ በተባበሩት መንግስታት የሚመራ የስደተኞች ካምፕ ነው ፡፡

አወር ከዓመት በኋላ ተወለደ ፡፡ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን እግር ኳስ በመጫወት አሳልፏል ፡፡ ባዶ እግሩን በአቧራማ ሜዳዎች ከወዳደቁ  ፌስታሎች በተሰራ የ‹‹ጨርቅ ኳስ›› ክህሎቱን አዳብሯል ፡፡

አወር 10 ዓመት ሲሞላው ቤተሰቦቹ ወደ አውስትራሊያዋ አዴላይድ አመሩ ፡፡ ወዲያውኑ አንድ ሃሳብ ወደ አዕምሮው መጣ ፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቱን እስከሚያሻሽል ድረስ በልጅነት መዝናኛው እና ፍቅሩ ራሱን መግለጽ እንደሚገባው አሰበ ፡፡ በእርግጥ በዚህ ወቅት የሚጫወተው በተገቢው ሜዳ እና ኳስ ነው ፡፡

እመርታው ድንቅ ነው ፡፡ መጀመሪያ ሰሞን በአካባቢው ለሚገኙ የተለያዩ ወጣት ቡድኖች ተጫወተ ፡፡ የጎል ዓይን ያለው የመስመር ተጫዋች ሆኖ ታየ ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በአካባቢው የሚገኘውን በከፊል ፕሮፌሽናል የሆነ ክለብ ካምፕቤልታወን ክለብ ተቀላቀለ ፡፡ በ16 ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ ፡፡ በተከታታይ ጨዋታዎች የተዋጣለት እንቅስቃሴ ማድረጉን ተከትሎ በላይኛው ሊግ በሚሳተፈው አዴላይድ ዩናይትድ የሚጫወትበት ዕድል አገኘ ፡፡

ማቢል በኤ-ሊግ መድመቁን ቀጠለ ፡፡ በመስመር በኩል ጥሩ ክህሎት እና ፍጥነት እንዳለው አስመሰከረ ፡፡ ኳስ ክሮስ የሚያደርግበት መንገድ ጥሩ ከመሆኑ በተጨማሪ ለጎል ዓይን እንዳለው አስመሰከረ ፡፡ በ2014-15 የውድድር ዘመን በ24 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ሰባት ጎሎችን አስቆጥሯል ፡፡ ዕድሜው ግን ገና በአስራዎቹ ውስጥ ነበር ፡፡

በባህር ማዶ የሚገኙ መልማዮች ተሰጥኦውን ልብ አሉ ፡፡ እ.አ.አ በሰኔ 2015 ወደ ዴንማርኩ ክለብ ሚቺላንድ ተዘዋወረ ፡፡ መጀመሪያ ሰሞን የመጫወቺያ ጊዜ ለማግኘት ተቸግሯል ፡፡ በውሰት ለሌኛው የዴንማርክ ቡድን ኤስበርግ እና ለፖርቱጋሉ ፓኮስ ደ ፌሬይራ ተጫውቷል ፡፡

ጎልቶ የወጣው እ.አ.አ በ2018 ነው ፡፡ ማቢል ወደ ሚቺላንድ ተመልሶ በመጀመሪያ ተሰላፊነት መጫወት ጀመረ ፡፡ ለአውስትራሊያ ዋናው ብሔራዊ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራው በዚያ ወቅት ነው ፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰልፎ በተጫወተበት ኩዌትን በገጠሙበት ግጥሚያ ጎል አስቆጠረ ፡፡

ለክለብ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ሆኖ ቀጥሏል ፡፡ በቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ ሆኗል ፡፡ ሚቺላንድ በ2019 የዴንማርክ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንዲያሸንፍ ረድቷል ፡፡ እ.አ.አ በ2020 ሊጉን እንዲያሸንፉ አግዟል ፡፡ መቢል ስምንት ጎሎችን አስቆጥሮ ስድስት ጎል የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል ፡፡

ሜዳ ላይ የሚያሳየው ጥረት የእርሱን ፈለግ ለመከተል ለሚፈልጉ ጥሩ መነሳሻ ይሆናል ፡፡ እንደ እርሱ ለመሆን ተስፋ ለሚያደርጉ ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ ማቢል ሜዳ ላይ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ በተጨማሪ በተግባር በስደተኛ ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ችግር ለመቅረፍ ጥረት አድርጓል ፡፡ ከወንድሙ ቡል ጋር በመሆን -‹‹ the Barefoot to Boots›› የተባለ የተራድኦ ድርጅት አቋቁመዋል ፡፡

ተቋሙ ለአስርት ዓመታት የእርሱ መኖሪያ በነበረው ካኩማ የተሰኘ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ይንቀሳቀሳል ፡፡ የትምህርት ፣ የጤና እና የጾታ እኩልነት ስራዎችን ይሰራል ፡፡ ቀዳሚው ትኩረቱ ግን እግር ኳስ ነው ፡፡ ይህ ጥረቱ በሙያ አጋሮቹ እውቅና ተሰጥቶታል ፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) እ.አ.አ ለማህበሩ “ከፍተኛ አስተዋጽኦ” የሚሰጠውን የ ‘ፊፋ ኦርደር ኦፍ ሜሪት’ ሽልማት እና 25 ሺህ ዶላር እ.አ.አ በ2018 አበርክቶለታል፡፡

የተራድኦውን ድርጅት በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት ኢያን ስሚዝ ናቸው ፡፡ የቀድሞ ክለቡ አዴላይድ ዩናይትድ የቦርድ አባል ናቸው ፡፡ ለመስመር ተጫዋቹ ያላቸውን አድናቆት በይፋ ከመናገር ተቆጥበው አያውቁም ፡፡ መቢል የፈጠረው ተጽዕኖ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ህይወት ለማሻሻል የተጫወተውን ሚና ከአውስትራሊያ ቴሌቪዥን ‘ኤስቢኤስ’ጋር ባደረጉት ቆይታ በዝርዝር ተናግረዋል ፡፡

‹‹ አወር ያሳካውን ነገር ሲመለከቱ ወጣቶች ህልማቸው እውን መሆን እንደሚችል እዲሰማቸው ያደርጋል ›› ይላሉ ስሚዝ ፡፡ ‹‹ ማምለጫ መንገድ ይሆናቸዋል ፡፡ ጠቀሜታውን ዝቅ ማድረግ አይቻልም ፡፡ የተለየ ወጣት ነው ፡፡ የአንበሳ ብርታት ታድሏል ፡፡ ልቡ የመልአክ ነው ፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል።

ማቢል ይህንን ብርታቱን እ.አ.አ በሰኔ ወር 2022 በሚገባ አሳይቷል ፡፡ አውስትራሊያ በሁለት አህጉራት ተወካዮች መካከል በተደረገ የማጣሪያ ጨዋታ ፔሩን ጥላ ወደ ካታር መጓዟን ስታረጋግጥ የእርሱ አስተዋጽኦ ወሳኝ ነበር ፡፡

በከፍተኛ ውጥረት የተደረገው ጨዋታ ጎል ሳይቆጠርበት ወደ መለያ ምት አመራ ፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያዎቹ አምስት የመለያ ምቶች አንድ አንድ ስተው እኩል ከሆኑ በኋላ ወሳኟን ስድስተኛ የመለያ ምት የመታው እርሱ ነበር ፡፡ ተረጋግቶ ኳሷን መረብ ላይ አሳረፈ ፡፡ የፔሩን የመጨረሻ ኳስ አሌክስ ቫሌራ መትቶ አንድሪው ሬድማይን አዳነ ፡፡ ሶከር ሩዝ ወደ ዓለም ዋንጫ መጓዛቸውን አረጋገጡ ፡፡

ይህ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የማቢል የተጫዋችነት ዘመን ጉዞ ትልቅ እመርታ አሳየ ፡፡ በስፔኑ ካዲዝ የአራት ዓመት ውል ተፈራረመ ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በመጨረሻዋ ዕለት መትረፉን ያረጋገጠው ቡድን በመልሶ ግንባታ ላይ ነበር፡፡

በላ ሊጋ ያሳለፈው የመጀመሪያዎቹ ወራት ቆይታ ቀላል አልነበረም ፡፡ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሳምንታት ማቢል በቂ የመጫወቻ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ ካዲዝ ግን የመጀመሪያዎቹን አምስት ጨዋታዎች ተሸነፈ ፡፡ ሌሎቹ አዲሶቹ ፈራሚዎች ብሪያን ኦካምፖ እና ቲዮ ቦንጎንዳ ከእርሱ ቀድመው ዕድል ይሰጣቸው ጀመር ፡፡ የቡድኑ ውጤትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ሄደ ፡፡ ከመስከረም ወዲህ ተሰልፎ የተጫወተው በአንድ አጋጣሚ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ነው፡፡

በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አራት ፈረንሳይ አውስትራሊያን 4 ለ 1 ስትሸነፍ ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ።

አውስትራሊያ ቱኒዚያን 1 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ በተመሳሳይ ከተቀያሪ ወንበር በመነሳት ሁለተኛ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል።በጥሎ ማለፉ አውስትራሊያ በአርጀንቲና 2 ለ 1 በተሸነፈችበት ጨዋታ በተቀያሪ ወንበር ላይ ነበር።

የካኩማ የስደተኞች መጠለያ

ዓለም ዋንጫው ለአወር ማቢል ልብን በሚያሞቀው ታሪኩ ሌላ ተጨማሪ ምዕራፍ የሚጨምርበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡

አወር ማቢል ለአውስትራሊያ ብሔራዊ ቡድን 30 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በእስከ አሁን የክለብ ቆይታው በ236 ጨዋታዎች 33 ጎሎችን አስቆጥሯል።

“እግር ኳስ የሕይወት መንገዴ ነው” የሚለው አወር ማቢል የእግር ኳስ ሕይወቱ ቀጣይ ምዕራፍ ላይ ምን አይነት ስኬቶችን ይጎናጸፍ ይሆን? ቀጣይ ዓመታት መልስ ይኖራቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም