ምሁራን በአገር ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

111

አዲስ አበባ (ኢዜአ)   ታህሳስ 22 ቀን 2015 ምሁራን በአገር ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ ገለጹ።

"የአገረ-መንግሥት ግንባታና የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የምርምር ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

በዛሬው እለትም የዚሁ መድረክ አካል የሆነ የውይይት መድረክ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ተካሂዷል።

በውይይቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ እንዳሉት፤ በውይይቶቹ ከ 500 ሺህ በላይ ምሁራን እንዲሳተፉ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመድረኮቹ ምሁራን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች እና እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዙን ገልጸዋል።

እንዲሁም ምሁራን የአገር ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ እንዲሁም ተሳትፏቸውን ከፍ እንዲያደርጉ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ዙር ውይይት በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከምሁራን ጋር የሚደረጉ መሰል ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በውይይቶቹ ከምሁራኑ ጋር በአገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአገር ደረጃ የተጀመረው የሰላም ግንባታ ሥራ ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲቀጥል ሚናቸውን እንደሚወጡ ስምምነት ላይ መደረሱን አመላክተዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው፤ መሰል መድረኮች ለአገር ግንባታ ሥራዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ምሁራን ያላቸውን እውቀት እና ሀሳቦች ለአገር ግንባታ በማዋል ሙያዊ እና የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአገር ግንባታ ላይ ምሁራን በዋናነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምሁራን ሥራዎችን ከንግግር ባለፈ በድርጊት በማሳየት ለተቀረው ትውልድ አርዓያ መሆን እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም