'ኢትዮጵያ ታምርት' አገር አቀፍ ንቅናቄ በሀረሪ ክልል በማምረት ላይ ያልነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ አስችሏል

120

ሐረር፣ ታህሳስ 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ታምርት አገር አቀፍ ንቅናቄ በሀረሪ ክልል በማምረት ላይ ያልነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማስቻሉን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡

 “የኢትዮጵያ ታምርት” አገር አቀፍ ንቅናቄ በሐረር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የሐረሪ  ክልል ርዕሰ  መስተዳድር  አቶ ኦርዲን በድሪና  ሌሎች ከፍተኛ የስራ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በመድረኩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ  ባለፉት አመታት በርካታ  ጫናዎች  ቢገጥሟትም  "የኢትዮጵያ ታምርት"  መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉ ይደርሱ የነበሩ የኢኮኖሚ ጉዳቶችን መቀነስ ተችሏል፡፡

ክልሉ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለይ ማምረት  ያቆሙ  ኢንዱስትሪዎች  ወደ ምርት  እንዲገቡ በስራ ላይ ያሉት ደግሞ ምርታቸውን  በማጎልበት   የአገር ውስጥ  ገቢ  እንዲጨምር  ማስቻሉን ገልፀዋል።

ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት አገራችን ያሏትን እምቅ ሃብቶች አልምታ  መጠቀም ያስፈልጋታል ያሉት አቶ ኦርዲን፤ ክልሉ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የመሰረተ ልማት፣ የመስሪያ ቦታ እጥረቶችን እየፈታ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ችግሮቹን ከመቅረፍ ባሻገርም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊ ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በሀረሪ ክልል በየቤቱ የሚመረቱ የእደ ጥበብ ስራዎችን በማሰባሰብ ምርቶች የሚሸጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ዘርፉ ከሃይል መቆራረጥ እና ሌሎችም ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንደሚፈቱ ገልጸዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ዩሱፍ በበኩላቸው በክልሉ 60 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ኢንዱስትሪዎቹ ብዙ ፈተና ተቋቁመው ማለፋቸውን ገልጸዋል።

በዘርፉ ለተሰማሩና አዳዲስ ለሚሰማሩ አልሚዎች ትኩረት በመስጠት የተመቻቸ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ሃይል ለማምረት ከማሰልጠኛ ተቋማት ጋር አብረው ለመስራት አቅደው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ችግሮቻቸውን እየፈታ ቢሆንም ቀሪ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በተለይ ከማምረቻ ቦታ ጋር እና ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለባቸው ችግር እንዲፈታ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም