በዞኑ ለቆላማ አካባቢዎች የሚስማሙ የአትክልት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ እየተሰራ ነው -- የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት

86
ማይጨው መስከረም 21/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ለቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ የስራስር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢኒስቲትዩቱ በራያ አዘቦ ወረዳ ባቋቋመው የሰርቶ ማሳያ ጣቢያ ያላመዳቸውን አዳዲስ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች ያስተዋወቀበት የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል ። በኢንስቲትዩቱ የመኾኒ ግብርና ምርምር ማዕከል ተወካይና የዘርፉ ተመራማሪ አቶ ጎበዛይ ሃፍቱ እንደገለጹት ማዕከሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባካሄደው የማላመድ ምርምር ቆላማ ለሆኑ የራያ አዘቦና የራያ አላማጣ ወረዳዎች የሚስማሙ የስራስር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎችን ለይቷል። "በማላመድ ምርምሩ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አምስት የድንች፣ አራት የቲማቲም፣ አንድ የበርበሬና 17 የፍራፍሬ ዝርያዎች ተለይተዋል" ብለዋል ። የድንች ዝርያዎቹ በሰርቶ ማሳያ ጣቢያ በሄክታር ከ200 እስከ 320 ኩንታል፣ የቲማቲም ዝርያዎቹ ከ289 እስከ 414 ኩንታል ምርት እንደሚሰጡ መረጋገጡን ተናግረዋል ። እንዲሁም በሄክታር 352 ኩንታል ምርት የሚሰጥ መልካ ዋዜ የተሰኘ የበርበሬና በሄክታር 332 ኩንታል ምርት የሚሰጡ  ዊልያምስ-1 እና ኒዚሩ የተሰኙ የሙዝ ዝርያዎች መመረጣቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። "አቦካዶና የሎሚ ዝርያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ዝርያዎችም መለየታቸውን የገለፁት ተመራማሪው ኢኒስቲትዩቱ ዝርያዎቹን በቅርቡ ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች የሚያሰራጭ መሆኑን ነው የገለጹት። ወረዳዎቹ ለስራስር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት አመቺ ቢሆኑም በአርሶ አደር ደረጃ በአመራረት ሂደት የሚያጋጥሙ የመስኖ አጠቃቀም ጉድለትና የምርጥ ዘር እጥረት እንዲሁም በሽታና ተባይ ለምርታማነት መቀነስ ምክንያት እንደሆኑ በጥናት መለየቱን ተመራማሪው ጠቁመዋል ። በትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ አሰፋ አስረስ በበኩላቸው ውጤታማ የሆኑ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ መምሪያው ከኢኒስቲትዩቱ ጋር እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በመስክ ጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የራያ አዘቦ ወረዳ ነዋሪ እርሶ አደር አፈራ ጎሮ በሰጡት አስተያየት በውስን ቦታ ላይ ፍራርሬ በማልማት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል መገንዘባቸውን ተናግረዋል ። ወደአካባቢያቸው ሲመለሱ ካላቸው የእርሻ መሳ ከፍለው ልማቱን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አርሶ አደሩ ገልፀዋል ። ወጣት አርሶ አደር ሻምበል ሐዲስ በበኩሉ ጉብኝቱ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በጓሮው ተክሎች ለማልማት መነሳሳት እንደፈጠረበት ተናግሯል ። በመስክ ጉብኝቱ ላይ 400 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል ፡፡                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም