የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የቻይና ኩባንያዎች ለአቅመ ደካማ ዜጎች ያስገነቧቸውን ቤቶች አስረከቡ

133

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015  የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ለሚኖሩ አቅመ ደካማና አረጋውያን ዜጎች ያስገነቧቸውን የመኖሪያ ቤቶች አስረክበዋል።

በመዲናዋ አዲስ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ለሚኖሩ አቅመ ደካሞች የተገነቡ አስራ አንድ የመኖሪያ ቤቶች ርክክብ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር  ለሊሴ ነሜ፤ በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ኩባንያዎች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ ሦስት የቻይና ኩባንያዎች ለአስራ አንድ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን የመኖሪያ ቤቶችን  በአጭር ጊዜ ገንብተው  ማስረከባቸውን በመጥቀስ፡፡

ኩባንያዎቹ ለአረጋውያኑ የቤት ቁሳቁስ፣ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ኮሚሽነሯ፤ ሌሎች ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች ሚኒስትር አማካሪ ያንግ ዪ ሃንግ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል መጠቀማቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባሻገር  ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት በኢንቨስትመንት ህብረተሰቡን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የማድረግ ሂደትን  በተግባር ለማሳየት ቁርጠኛ መሆናቸውንም እንዲሁ።

ቤታቸውን የተረከቡ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች በበኩላቸው የመኖሪያ ቤታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ባማረ ሁኔታ ተገንብቶ በመረከባቸው ደስታቸውን በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም