የወጣቶች እምቅ አቅምና ልዩ ችሎታ ለአገር ልማት ለማዋል የልዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ማስፋት ያስፈልጋል

217

 አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2015 (ኢዜአ)  የወጣቶች እምቅ አቅምና ልዩ ችሎታ ለአገር ልማት ለማዋል የልዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ማስፋት ይገባል ሲሉ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሳይበር ደህንነት 'በሳመር ካምፕ ፕሮግራም'  ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 60 ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶችን ዛሬ አስመርቋል።

ተመራቂዎቹ ስልጠናቸውን በ2014 ዓ ም የክረምት ወቅት ለአንድ ወር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።

በምረቃው ወቅት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፤ የወጣቶችን እምቅ አቅምና ልዩ ችሎታ ለአገር ልማት ማሳለጫ ለማዋል በዝንባሌያቸው መሰረት ስልጠና መስጠት ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ በመላው አገሪቱ የልዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ማስፋት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ደህንነት ማዕከል አቋቁሞ ለመጀመሪያ ጊዜ 60 ተማሪዎችን ማስመረቁ የሚበረታታ ጅምር ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን ካለን የህዝብ ቁጥር አንጻር በቂ ባለመሆኑ  ማዕከሉን በመላው አገሪቱ በማስፋት ከዚህ የበለጠ መስራት እንደሚገባ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩለቸው፣ በራስ አቅም የለማ ቴክኖሎጂ መጠቀም ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ፡፡

እንደ አገር የራሳችንን ቴክኖሎጂ ለማበልጸግ ወጣቶችን በዝንባሌያቸው መሰረት ስልጠናዎችን የመስጠት ተግባር ሁነኛ መንገድ ነው ብለዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለሚያከናውነው የባለልዩ ተሰጥኦ ወጣቶች አዕምሮን የማልማት ተግባር ሚኒስቴሩ የሚጠበቅበትን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው  ተቋሙ የበለጸገች እና ብሔራዊ ደህንነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የባለልዩ ተሰጥኦ ወጣቶችን አዕምሮ የማልማት ስራ እየተሰራ ነው።

ተቋሙ የባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶች  የሳይበር ደህንነት የሳመር ካምፕ ፕሮግራም ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር እየሰራ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

ታዳጊዎች ከተመረቁ በኋላም የፈጠራ ስራዎቻቸውን ባለሃብቶችና ተቋማት እንዲጠቀሙት ለማድረግ የትስስር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተመራቂዎች በበኩላቸው በስልጠና ቆይታቸው የተለያዩ እውቀቶችን ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀጣይም በቴክኖሎጂው ዘርፍ አገሪቱን ወደ ፊት የሚያራምድ ተግባር ለመከወንና  ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም