የሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠንና እጥረት ጥልቀት ባለው የጥናትና ምርምር ፖሊሲ መመለስ ይገባል-ባለሙያዎች

68
አዲስ አበባ መስከረም 21/2011 የሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠንና እጥረት እያስከተለ ያለውን የጤና ችግር ጥልቀት ባለው የጥናትና ምርምር ፖሊሲ መመለስ ይገባል ሲል  የኢትዮጵያ ምግብ ባለሙያዎች ማህበር ገለጸ። ማህበሩ ከአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብ ማህበርና ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትጋር በመተባበር ስምንተኛውን 'የአፍሪካ ኒውትሪሽን ኢፒዶሞሎጂ' ጉባዔ "ባለድርሻ አካላት ለተቀናጀ ስነ ምግብ ትግበራ፤ ጥናቶችን ለውጤታማ ፖሊሲና ፕሮግራም ቀረፃ ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ምግብ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ቀልቤሳ ኡርጋ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካና በኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ እጥረትና አለመመጣን የተለያዩ አይነት የጤና ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል። የስርዓተ ምግብ እጥረት በህፃናት እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖና የመቀንጨር ችግር እያስከተለ ሲሆን ያልተመጣጣነ የስነ ምግብ ሥርዓት ደግሞ ህዝቡን ለስኳር፣ ለካንሰር፣ ለልብና ለመሳሰሉት ችግሮች እየዳረገው ነው። በመሆኑም የስርዓተ ምግብ ችግሩን ከህብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታና ባህል ጋር የሚናበብ እንዲሁም ጥልቅ ጥናትና ምርምር መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ነድፎ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት በስርዓተ ምግብ ረገድ በተሰሩት ሥራዎች ውጤቶች መመዝገብ ተጀምራል ብለዋል። በተለይ የስርዓተ ምግብ እጦት ችግር ለመፍታት ከሶስት ዓመት በፊት የሰቆጣ ቃል ኪዳን/ ስምምነት/ መፈረሙን ጠቁመው በአማራና በትግራይ ክልል በተሰራው ሥራ የአቀንጭራ ችግር እየቀነሰ መጥቷል። ይህም ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2030 ድህነትን ለመመቀነስና አስከፊ ረሃብን ለማጥፋት እየተደረገ ላለው ጥረት አስተዋጾኦው የጎላ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ጉባዔው በጥናትና ምርምር ላይ መመስረቱ የባለሙያዎችን አቅም ከመገንባት ባለፈ ለፖሊሲ ቀረፃ የሚሆኑ ግብዓት የሚገኝበት መሆኑን ጠቅሰዋል። የአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አሞስ ላር ደግሞ ጉባዔው በየሁለት ዓመቱ እንደሚዘጋጅ ተናግረው ይህም በአፍሪካ በስርዓተ ምግብ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታትና ለፖሊሲ አውጪዎች ያሉትን አማራጮች ለማመላከት ያለመ ነው ብለዋል። በተለይም በኢትዮጵያ ስላለው የስርዓተ ምግብ ልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም የሌሎች አፍሪካ አገራት ተሞክሮ ለመቅሰም መሆኑንም አክለዋል። ስለሆነም በምግብ ደህንነት፣ በምግብ ኢንዱስትሪ፣ ከምግብ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ምግብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሰሩ ምርምሮቾና ጥናቶች ይቀርባሉ ሲሉም አብራርተዋል። ጉባዔው ለቀጣዮቹ አራት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን ከአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ መሪ ተመራማሪዎችን ጨምሮ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም