የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በተሻለ መንገድ ለመገንባት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ገለጸ

167

ሰቆጣ አዲስ አበባ ታህሳስ 20 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአማራ ክልል የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በተሻለ መንገድ ለመገንባት የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር ገለፁ።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በጦርነቱ የወደሙ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የመልሶ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት፤ በጦርነቱ ምክንያት ውድመት የደረሰባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት መልሶ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነው።

ሰላምን ለማምጣት የነበረውን ፅናትና ቁርጠኝነት ልማትን ለማረጋገጥም መድገም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት የወደሙ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በጀት መድቦ እየሰራ እንደሆነ በማብራራት።

በቀጣይም የወደሙ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን ወደ ቀደመ አገልግሎታቸው በተሻለ መልኩ ለመገንባት ክልሉ ህዝቡንና የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችንና በጦርነቱ ቤታቸው የወደመባቸው ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ የሚደረገውን የመልሶ ግንባታ ሂደት ህዝቡ፣ ባለሃብቱና ድርጅቶች በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።



የብሄረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ስቡህ ገበያው እንዳሉት የክልሉ መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ የብሄረሰብ አስተደሩ መልሶ ግንባታ የሚውል 120 ሚሊየን ብር በመደብ የመልሶ ግንባታ ስራው በመጀመሩ ምስጋና አቅርበዋል።

ህዝቡ አሁን በመጣው ሰላም መሰረት ፊቱን ወደ ልማት አዙሮ ህይወቱን ለመቀየር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደ ከንቲባ አቶ መላሽ ወርቃለማው በበኩላቸው በከተማው ጤና ጣቢያን ጨምሮ ትምህርት ቤትና የግለሰቦች መኖሪያ ቤት የመልሶ ማቋቋም ስራ መጀመሩ ህዝቡን ወደ ቀደመ ህይወቱ ለመመለስ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

በቀጣይም በከተማው የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ህዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ከተማ አስተዳደሩ የማስተባበር ስራ ይሰራል ብለዋል።

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ የክልሉ፣ የብሄረሰብ አስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም