በመቀሌ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ተጀመረ

275

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ 19/2015 መንግስት ቃል በገባው መሰረት በመቀሌ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ኩባንያው እስካሁን የሰራቸውን ተግባራት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም መንግስት ቃል በገባው መሰረት ተቋርጠው የቆዩ የመሰረት ልማት አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲጀመሩ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት በመቀሌ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት መጀመሩን ገልጸዋል።

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች በርብርብ በመጠገን ወደ አገልግሎቱ እንዲጀመር ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም እስካሁን 981 ኪሎ-ሜትር የፋይበር ጥገና መደረጉን ገልጸው በትግራይ ክልል እስካሁን 27 ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በተለያዩ ከተሞች 61 የባንክ ቅርንጫፎች ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በዛሬው ዕለትም የመቀሌ ከተማ ዳግም የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘቷን ጠቁመዋል፡፡

በዋናነት አሁን ላይ ወደ አገልግሎት የገባው የድምጽ አገልግሎት መሆኑን የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ በቀጣይ ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ሱቆችና ሌሎች አገልግሎቶች ወደ ስራ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለረጅም ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው የሲም ካርዳቸው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበት በመሆኑ ከማዕከል የአገልግሎት ዕድሜውን የማራዘም ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ተከትሎ መንግስት የቴሌኮም፣ መብራት፣ የባንክ፣ የአየር ትራንስፖርትና ሌሎችም አገልግሎቶች በማስጀመር የተጠናከረ የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገም ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም