''የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለሌሎች የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መልካም ተምሳሌት ነው'' - አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ

186

ታኅሣሥ 19 / 2015 (ኢዜአ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውውይታቸው ወቅት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት አህጉሪቱ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የያዘችው መርህ ውጤት እያስመዘገበ ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አቶ ደመቀ ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መጥተዋል ነው ያሉት።

ከአሁን በፊት ግጭቱ ተከስቶባቸው በነበሩ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በግጭቱ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶችም ዳግም እየጀመሩ መሆናቸውን ለኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

መንግሥት ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ግቢራዊነት ሙሉ ቁርጠኝነት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ ለሌሎች የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መልካም ተምሳሌት መሆኑን አንስተዋል።

አምባሳደር ባንኮሌ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተሞክሮ በቀጣይ በአዲስ አበባ በሚደረገው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በተሞክሮነት እንደሚቀርብ ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ከመሠረቱ ጀምሮ ለአፍሪካ ሕብረት የሰጠው ጽኑ አቋም ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው ነው ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እና በመሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀምሩ በማድረግ የታየው ተግባራዊ ሥራ የሚያስመሰግን መሆኑን መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም