በአሰቃቂ የግድያ ወንጀል የተከሰሱ አራት ግለሰቦች እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

95

አሶሳ ፤ ታህሳስ 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንዲት ግለሰብን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ወንጀል የተከሰሱ አራት ግለሰቦች እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ አምነላ ሰበባ እንደገለጹት፤ ተከሳሾቹ በአሶሳ ከተማ ወረዳ አንድ ቀጠና 2 በተለምዶው ጫት ተራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት በአንዲት ግለሰብ መኖሪያ ቤት በመግባት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ መግደላቸውን በአቃቤ ሕግ ማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል።

ተከሳሾቹ ግድያውን ከፈጸሙ በኋላ ከ37 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የሟች የቤት ንብረቶች መዝረፋቸውንም አመልክተዋል።

አቃቢ ህግ ግለሰቦቹን በአሰቃቂ የግድያና የዘረፋ የወንጀል ድርጊት በማስረጃ አስደግፎ የመሰረተባቸው ክስ እንዲከላከሉ እድሉ ቢሰጣቸውም እንዳልቻሉ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል።

በወንጀል የተከሰሱት አንደኛ ድባቤ ታየ፣ ሁለተኛ መሃመድ ነጉራ፣ ሶስተኛ ሙስጣፋ አበራ እና አራተኛ ሃሊማ ሽባነ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በአራቱ ተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቀዋል።

በዚህም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሽ እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ላይ የ20 ዓመት ጽኑ እስራት እና አራተኛ ተከሳሽ ደግሞ በአንድ ዓመት ጽኑ እስራት እና በአንድ ሺህ ብር እንደትቀጣ መወሰኑን የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም