በኢሬቻ በዓል ላይ የሌሎች ብሄረሰቦች አባላት ጭምር መታደማቸው አገራዊ አንድነትን ያጠናክራል

87
ቢሾፍቱ መስከረም 20/2011 በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ በሚሰጠው የዘንድሮው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች መታደማቸው አገራዊ አንድነት እንደሚያጠናክር ተገለጸ። የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በተገኘበት በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ሀይቅ  በደማቅ ስነ-ስርዓት ዛሬ ተከብሯል። የዘንደሮው በዓል ከዚህ ቀደሞቹ ከነበሩት መሰል በዓላት በተለየ በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮችም ታድመውበታል። በበዓሉ ላይ በተለይ ከሲዳማ፣ ቡርጂ፣ ሀላባ፣ ኮንሶና ጋሞ ብሄረሰቦች የተወከሉ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተገኝተዋል። የዚህ ዓይነቱ  ማህበረሰባዊ መስተጋብር በአገሪቱ ህዝቦች መካከል ያለውን መቀራረብ ለማጠናከርና የጋራ እሴትን ለመገንባት የተጀመሩትን እንቅስቃሴዎች እንደሚያግዝ ነው የተገለጸው። የብሄረሰቦቹ አባላት የበዓሉ ተሳታፊ መሆናቸው በህዝቦች መካከል የባህል ልውውጥን ለማዳበርና የተሻለ መቀራረብና መተሳሰብ ለመፍጠር ዓይነተኛ አጋጣሚ መሆኑን ኢዜአ ያነጋራቸው እነዚሁ ታዳሚያን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የተዋጣለት ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ እድገትን ለማረጋገጥ ቁልፍ የሆነውን አንድነት ለማጠናከርም የዚህ ዓይነቱ መስተጋብር እግዛ እንዳለው የብሄረሰቦቹ አባላት ገልፀዋል። በመሆኑም በመላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚከወኑ ሌሎች መሰል ኩነቶች ላይም የዚህ ዓይነቱ ተግባር ሊለመድ እንደሚገባ ያሳስባሉ። እድሉን አግኝተው የበዓሉ ታዳሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በክብረ በዓሉ ስነ-ስርዓት ከመደመም ባሻገር የተደረገላቸውን መስተንግዶም አድንቀዋል። አቶ መሐመድ ወሌ የቡርጂ ብሄረሰብ ተወካይ ''እዚህ ከመጣን በኋላ ፍቅር፣ አንድነትን፤ መደመር የሚባለው ነገር በእውን መደመር መሆኑን ነው  የተረዳነው፤ በህላችንንም በጥምረት እኛም በምንጋብዝ ጊዜ ብዙ የኦሮሞ ወንድሞቻችን መጥተው ባህላችን ላይ እንደሚገኙ ተስፋ በማድረግ ነው፤ በጣም ደስታችን ከልክ በላይ አልፎ ነው ያለው” በማለት ገልጸዋል፡፡ አቶ ዑመር ሁሴን የቡርጂ ብሄረሰብ ተወካይ እንደተናገሩት ''እኛም የቡርጂን ህዝብ ወክለን ስንመጣ ከኦሮሞ ብሄረሰብ ጋር በታሪክ የተገናኘን፤ የተቆራኘን ብሄረሰብ ነን፤ በተለይ ከቦረና ጋር አንድ ሆነን ከሊበን ተነስተን አብኖ ገብተን ቋንቋችን ተለያየ እንጂ ባህላችንና ሁሉነገራችን አንድ ነው።ስለዚህ እዚህ ከመጣን በኋላ ይሄን ሁሉ ህዝብ ስናገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ከኦሮሞና ቡርጂም አልፎ አንድነት እንደሚጠናከር ነው፤ ለዚች አገር ለመኖር አንድነት ወሳኝ ስለሆነ ከዚህ ህዝብ ጋር ተደምረን አንድ ሆነን እንድንሄድ ነው የምንፈልገው” ብለዋል፡፡ አክለውም በመሃከላችን አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮች በጋራ በመፍታት እንደዚህ በመቀራረብ እንዲሰራ ምኞታችን ነው ብለዋል፡፡ ወጣት አማኑኤል እንድሪያስ የሲዳማ ብሄር ተወካይ በበኩሉ ሲዳማና ኦሮሞ ትልቅ ታሪክ ያለን ሰዎች ነን፤  ከዚህ በኋላ ያለን አንድነታችንን እንቀጥላለን በመቀጠል  አስተባብረን  ወደዚህ ሁሉም እንዲመጣ እንደምናደርግ እገምታለሁ ብሏል፡፡ የኢሬቻን በዓል ለማክበር በጉጉት ስንጠብቀው ነበር ያሉት ሌላው አቶ ደሳለኝ ጭንቅሳ የሲዳማ ብሄር ተወካይ  ወደቦታው ትናንት መምጣታቸውን ገልጸው  ቄሮዎች በደብረ ዘይትም ፤ ሞጆም ላይ በጥሩ ሁኔታ ተቀብለው ማስተናገዳቸውን ያስረዱት አቶ ደሳለኝ ጭንቅሳ የሲዳማ ብሄር ተወካይ ናቸው፡፡ በዓሉ ለኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊም በጣም ጠቃሚ ነው ብለው ለአንድ ዓላማ አንድ ላይ ሆነን ተቀራርበን አገራችንን በአንድነት ለማልማት ይጠቅማል በማለት ገልጸዋል፡፡ ወዳጅ መሐመድ ሀላባ ብሄረሰብ ተወካይ  ከአሁን በፊት በሚዲያዎች የሚሰሙትን በአሁኑ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ ባመጡት ለውጥ ተደምሬን መደመራችንን ደግሞ የመጀመሪያው በእሬቻ በዓል ላይ ተገኝተን በመሳተፋችን በጣም ደስ ብናል ብለው ከዚህ ቦኃላም መደመራችንን በአንድነት አጠናክረን ለማስቀጠል ተስፋ እንዳላቸውም አብራርተዋል፡፡ በየዓመቱ የመስቀል በዓልን ተከትሎ በሚመጣው እሁድ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የዘንደሮው ክዋኔ በታላቅ ድምቀት በሰላም ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም