ብአዴን ስያሜውን ቀየረ

61
ባህርዳር መስከረም 20/2011 የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን ስያሜውን አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ በሚል መቀየሩን አስታወቀ። በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሜቴ ጽህፈት ቤት የገጠር ፖለቲካና አደረጃጀት እና የ12ኛው ጉባኤ ቃል አቀባይ አቶ ምግባሩ ከበደ ማምሻውን እንደገለፁት ጉባኤው በዛሬው ውሎ የድርጅቱ ስያሜና አርማ ላይ ለውጥ አድርጓል። በዚህም የድርጅቱን ደረጀ፣ አካታችነትና የአማራን ህዝብን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ገምግሞ ስያሜውን መቀየሩን ተናግረዋል። እንዲሁም የድርጅቱን አርማም አርንጓዴ፣ ወርቃማ ቢጫና ቀይ መደብ በማድረግ ቀደም ሲል ከነበሩት ምልክቶች ላይ የአባይ ወንዝ እንዲካተት መደረጉን አመልክተዋል። የድርጅቱ ልሳን ጋዜጣ ስያሜም በአዲስ መልክ በሚቋቋመው ማዕከላዊ ኮሚቴ ተገምግሞ አዲስ ስያሜ እንዲሰጠው አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁመዋል። በተሻሻለው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረትም የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የአባላት ምልምላ የፓርቲውን ፕሮግራም የሚቀበልና በክልሉ ውስጥ የሚኖር አማራ፣ አገው፣ ዋግ፣ አሮሞ፣ ቅማንትና አርጎባ የሆነ ሁሉ አባል መሆን እንዲችል ተደርጓል። እንዲሁም ከክልሉ ውጭ የሚኖር የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሮግራሞችን አምኖ መቀበል የሚችልም በአባልነት ተመዝግቦ መንቀሳቀስ እንደሚችል ቀደም ሲል የነበረው መተዳደሪያ ደንብ እንዲቀጥል ተወስኗል። የጥረት ሃብት ቀደም ሲል 11 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሎ በቀድሞ አመራሮች የተገለፀው ስህተት መሆኑንና በተደረገ የሃብት ቆጠራም ከ50 በመቶ በታች ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል። በጥረት ለኪራይ የሚውሉት ተሽከርካሪዎችም 70 በመቶ ከሦስተኛ ወገን የሚቀርቡ ሆነው መገኘታቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለ አመልክተው ከ500 በላይ መኪናዎች አሉ የተባለውም ከ250 እንደማይበልጡ አብራርተዋል። 12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ ባደረገው ውሎም የስራ አፈፃፀምና የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርትን በማፅደቅ የሪፖርቱ አንዱ አካል ማድረጉን ጠቁመዋል። ጉባኤው ማምሻውን ድርጅቱን በቀጣይ ሊመሩ የሚችሉ የማዕከላዊ ኮሚቴና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን በመመልመል በትምህርትና ዲሲፕሊን ግድፈት የሚሰናበቱ አባላትንም በክብር ሊሸኝ ይችላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም