ቻይናን ሳስባት

419

(በረከት ሲሳይ)

አፈሩን ያቅልልላቸውና በቅርቡ በሞት የተለዩን አምባሳደር እምሩ ዘለቀ ከዓመታት በፊት በአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ቀርበው በ1960ዎቹ ወደ ቻይና በማምራት፤ ሆንግ ኮንግን ጨምሮ የተለያዩ የቻይና ከተማዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን በመግለጽ፤ በዚያን ጊዜ ቻይና የነበረችበትን የድህነት ሁኔታና አሁን ላይ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ በማነጻጸር የነበራቸው አድናቆትና ግርምት አሁንም ይታወሰኛል። አለፍ ብለውም ቻይና ከ1970ዎቹ ጀምሮ ባልተቋረጠ የዕድገት ምህዋር ውስጥ በመግባት ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበችበትን  ሂደት ከኢትዮጵያ ጋር በትይዩ በማነጻጸር “እኛን ምን ነክቶን ነው?” በማለት አምባሳደሩ በቁጭት ያነሱት ጥያቄ ከዓመታት በኋላ ዛሬ ላይ እኔ በድጋሚ ላነሳው እወዳለሁ። ለአምስት ወራት ገደማ ለሙያ ሥልጠና በከረምኩባት የሩቅ ምስራቋ “ቻይና” በእውነቱ! ዕድገቷን አይቶ “እኛስ መቼ ነው እንዲህ የምንሆነው?” ብሎ አለማሰብ ከቶ አይቻልም። በዚህ ተጠየቅ፤ በቻይና በሄድኩባቸውና በደረስኩባቸው ከተሞች እንዲሁም በጎበኘኋቸው ተቋማት ሁሉ በዓይነ-ህሊናዬ ኢትዮጵያን እያሰብኩኝ ቆይታዬን አገባድጄ በቅርቡ ወደ አገሬ ተመልሻለሁ።

ወረርሽኙና ቆይታዬ

በቻይና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር በሚንቀሳቀሰው የቻይና ዓለም አቀፍ የፕሬስ ማዕከል ጋባዥነት ነበር ለአራት ወር ተኩል የሥልጠና ቆይታ ወደ ቻይና ያመራሁት። ሥልጠናው እኔን ጨምሮ ከ60 በማደግ ላይ ያሉ አገራት የተውጣጡ 75 ጋዜጠኞችን ተሳታፊ ያደረገ ነበር። ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለበርካታ ተጓዞች ወደ ቻይና መግባት ከባድ በሆነበት ወቅት ሥልጠናው መካሄዱ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንድጋፈጥ አስገድዶኛል። ቻይና ከመግባቴ በፊት በአዲስ አበባ ለአምስት ቀናት እንዲሁም ቻይና ከደረስኩ በኋላ ሥልጠናው በዋነኝነት ወደሚካሄድባት የቻይናዋ ርዕሰ ከተማ ቤጂንግ ከማቅናቴ በፊት ደግሞ በደቡባዊ ቻይና በምትገኘው ጓንዙ ከተማ ለአሥር ቀናት በድምሩ ለ15 ቀናት ተከታታይነት ያለው የኮሮና ምርመራ በማድረግ ወሽባ (ኳራንቲን) ውስጥ ማሳለፌ ከገጠሙኝ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንደኛው ነው። ምንም እንኳን ከኮቪድ ነፃ መሆኔ ተረጋግጦ ወደ ቤጂንግ ባቀናም አገሪቱ ወረርሽኙን ለመከላከል ያወጣችውን ፖለሲ ተከትሎ ሥልጠናውን አጠናቅቄ እስከምመለስበት ጊዜ ድረስ በየሁለት ቀናት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ መገደዴም ሌላው የገጠመኝ ፈተና ነበር።  

ቻይና ከመግባቴ አስቀድሞ በተለይም ስለ ወረርሽኙ ሁኔታና ቁጥጥር በተመለከተ ከነበረኝ ግንዛቤ በተጨማሪ ከሚመለከታቸው አካላት ገለጻ ቢደረግልኝም፤ በመጀመሪያዎቹ ቀናት መደናገር አልቀረልኝም። ነገሮች አዲስ ሆነውብኛል፤  በየሁለት ቀናቱ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በመደበኛነት ማድረግ፣  የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግ፤ ወደየትኛውም የሕዝብ መገልገያ ሥፍራ ማለትም መዝናኛ ቦታዎች፣ ሱፐር ማርኬትና ሌሎች ሥፍራዎች ለመገኘት በእጅ ስልክ ላይ ባለው መተግበሪያ (ቢጂንክ ሄልዝ ኪት) አማካኝነት የምርመራ ውጤት በር ላይ ላሉ አሳላፊዎች ማሳየት በግዴታነት መቀመጡ ከነበረኝ ልምድ ጋር ፍጹም የተለየ ነው። ነፃ የምርመራ ውጤትን ሳያሳዩ የትም መግባትም ሆነ መንቀሳቀስ አይታሰብም። ጎን ለጎንም በርካታ ለወረርሽኙ አጋላጭ ናቸው የተባሉ የሕዝብ መሰብሰቢያ ሥፍራዎች ዝግ ናቸው፤ መዝናኛ ቦታዎችና የሕዝብ መገልገያ ማዕከላት ከመደበኛው ታዳሚዎቻቸው በእጅጉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ብቻ እንዲያስተናግዱ ተገደዋል፤  በአገሪቱ የሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች ላይም እገዳ ተጥሏል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች አገራት ወደ ቻይና የሚጓዙ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ወደ ቻይና የሚያደርጉት ጉዞ በወረርሽኙ ሳቢያ መስተጓጎል ገጥሞታል። በውጭ የሚኖሩ ቻይናውያንም በወረርሽኙ ምክንያት እንደልባቸው ተመላልሰው የአገራቸውንና የወገናቸውን ናፍቆት መወጣት እንዳይችሉ ሆነዋል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች ቀርበን ያወጋናቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቻይና ቁጥጥሩን በእጅጉ ብታላላው በርካታ ዜጓቿን በሞት ልታጣ እንደምትችል ጥናት አጣቅሰው አስረድተውናል። በመሆኑም ወረርሽኙን ለመከላከል የተተገበረው ፖሊሲ አገሪቱ ውድ የሆነውን የዜጎቿን ህይወት እንድታተርፍ ከማስቻሉ ባለፈ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገቷ ተጽዕኖዎችን ተቋቁሞ በአዎንታዊ የዕድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገሰግስ እንዳስቻላትም ያትታሉ።

ያም ሆኖ አገሪቱ ወረርሽኙን ለመከላከል የመደበችው የሰው ኃይልና የምታፈሰው ገንዘብ እጅግ በርካታ መሆኑን ሳስብ እንዲሁም ሕዝቡም ሳያወላውል ወረርሽኙን ለመግታት የወጡ ደንቦችን በማክበርና በመተግበር የተወጣው አስተዋፅኦ እጅግ ያስገርማል። ወረርሽኙን ለመከላከል የሄዱበት ርቀት ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ለመከወን የሚቻልም አይደለም።  

ወደ ቀድሞ ነገር ስንመለስ- በዚህ አውድ ውስጥ የተካሄደው ይህ የጋዜጠኞች ሥልጠና በመደበኛነት የቻይና ታሪክ፣ ባህል፣ ማኅበራዊ አወቃቀር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓትና በአንዳንድ የጋዜጠኝነት ርዕሰ- ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። በተለይም የቻይናን አሁናዊ ሁኔታ እንድንረዳ ያለመ ሲሆን ወረርሽኙን ታሳቢ በማድረግም በሰሜኑና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ አምስት ግዙፍ ከተሞች ጉብኝት አድርገናል።  

በጎበኘናቸው እያንዳንዱ ከተሞች እጅግ የሚያስደምሙ የመንገድ፣ የወደብ፣ የኤርፖርት፣ የባቡር መስመርና ጣቢያ፣ መዝናኛ ሥፍራዎችና ሕዝባዊ ተቋማት የመሰሉ አስደማሚ መሰረተ-ልማቶችን ተመልክተናል። የኢንዱስትሪ ልማትና ስፋት፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና የተቋማት ግንባታው ቀልብን ይገዛል። የከተሞቻቸው ስፋትና መሰረተ-ልማት እንዲሁም ሌሎች የአገልግሎት አቅርቦቶች ዜጎቻቸው በምቹ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። በጎበኘናቸው የገጠር አካባቢዎችም ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዜጎች ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምሩ የሚሰራውን ሥራ በዚያው ልክም ገቢያቸው እያደገ የተሻለ ህይወት እየመሩ መሆኑን ተመልክተናል። በሌላ በኩል በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተለይም በፈጠራ ሥራ አስደማሚ ሥራዎችን በመሥራት አገራቸው ሌላ ገጽታ እንዲኖራት ማስቻላቸውንም እንዲሁ።

የቻይና ዕድገት

የቻይና ዕድገት ከማንም የተሸሸገ ባይሆንም “ማየት ማመን ነው” እንደሚባለው በአካል ተገኝቶ አሁን ላይ አገሪቷ የደረሰችበትንና ቀድሞ የነበረችበትን ሁኔታ ማነጻጸር መቻል በራሱ ብዙ ያስተምራል። ቻይና ባለፉት 40 ዓመታት 800 ሚሊዮን ሰዎችን ከድህነት በማላቀቅ ቀዳሚ ተደርጋ የምትነሳ አገር ናት። በ1960ዎቹ አገራዊ ጠቅላላ ምርቷ ከጎረቤት አገራችን ከኬንያ በታች የነበረ ሲሆን፤ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በአማካኝ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021፤ 17 ነጥብ 73 ትሪሊየን ዶላር ጠቅላላ አገራዊ ምርት በመያዝ ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። እጅግ የከፋ ድህነት ውስጥ የነበሩት ቻይናውያን አሁን ላይ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው 10 ሺህ ዶላር ደርሷል። ቻይና በቀጣይ 13 ዓመታት የዜጎችን ገቢ 20 ሺህ ዶላር ለማድረስ ያለመታከት እየለፋች ትገኛለች። ቻይና አሁን እየሄደች ያለችበት የዕድገት ፍጥነት በተለይም ጠቅላላ የአገራዊ ምርት ደረጃዋ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአንደኝነት ደረጃን ከአሜሪካ እንድትረከብ ያስችላታል የሚሉ በርካታ ተንታኞች አሉ። በተቃራኒው በ1990ዎቹ ጃፓንም አሜሪካን በዕድገት ትቀድማለች ተብሎ ሳይሳካ መቅረቱን አንስተው፤ ይህንን መላምት ውድቅ የሚያደርጉ ተከራካሪዎችም አሉ።

የቻይና ምጣኔ ሀብታዊ ግስጋሴ በጣም ፈጣን የሚባልና ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ መሆኑ በዘርፉ ብቸኛዋ አገር ያደርጋታል። በተለይም ከሁለት ዓመታት በፊት የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምጣኔ ሀብቷን እስኪፈትነው ድረስ የአገሪቱ የዕድገት ሂደት ወጥ የሚባል ነበር ማለት ይቻላል።  ቻይና እንዴት አደገች? ለሚለው ጥያቄ በርካታ የመስኩ ተንታኞች እንደሚያስቀምጡት፤ የቻይና ዕድገት “የኢንዱስትሪ መር” መሆኑን ያለልዩነት ይስማሙበታል። የቻይና መንግሥት አገሪቱን ለውጭ ገበያ እንዲሁም ለውድድር ክፍት ካደረገበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1978 ጀምሮ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ጀምሮ አሁን ላይ እስከተገነቡ ግዙፍ ኩባንያዎች ድረስ ለኢንዱስትሪ ልማት የተሰጠው ትኩረት እጅጉን የሚያስገርም ነው።

አገሪቱ በተለይም በገጠሩ የማኅበረሰብ ክፍል የግብርና ምርትን በማስፋፋት ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የምርት ሽያጭ ዋጋን ከፍ በማድረግ ትልቅ ሥራ ሰርታለች። በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የተጀመረው የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ መርሃ-ግብርም ትልቅ እመርታን ማስመዝገብ አስችሏል።  የኢንዱስትሪ ምርቶች የገበያ ተደራሽነታቸውን በማስፋት መንግሥት የሰጠው ከለላም ኢንዱስትሪዎቹ በእጅጉ እንዲያድጉ አድርጓል። ከዚያ በመለስ የቻይና የልማት ዕቅድ ውስጥ “ፈጠራ” ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የኢንዱስትሪና የምርምር ተቋማት በዚሁ ጉዳይ ላይ እንዲሰሩና የተሻሉ ውጤቶችን እንዲያመጡ አስችሏቸዋል።

ዛሬ ላይ የቻይና ኢንዱስትሪዎች የውስጥ ፍላጎትን ከማዳረስ አልፈው ለሌሎች የዓለም አገራትም ተርፈዋል። በፈጠራ ሥራ ላይ ያስመዘገቧቸው ለውጦችም በተለይም በታዳጊ አገራት ላይ ቻይና ያላት ተጽዕኖ ከፍተኛ እንዲሆን አስችሏል። በሌላ በኩል ቻይና ጠንካራ መንግሥታዊ አመራርና ተከታታይነት ያለው ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረጓ ለዚሁ መብቃቷም ይጠቀሳል። የሕዝቡ ፅናትና ቆራጥነትም ለዚህ ውጤት ጉልህ ሚና አለው። በተለይም ከ1970ዎቹ በፊት በነበሩት ጊዜያት የነበረው ድህነት ከባድ መሆኑን በማንሳት ቻይናውያን አንድም ወደ እዚያ ሕይወት ዳግም ላለመመለስና ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር የነበራቸው ተነሳሽነት በሌላ በኩል ደግሞ ለቀጣይም ትውልድ የተሻለ አገር ለማስረከብ የነበራቸውን ቁርጠኝነት ለዕድገታቸው በምክንያትነት ያነሳሉ።

ምን እንማር

መቼም ከድህነት እስካልወጣንና የራሳችንን ዕድገት በራሳችን ጥረት እስካላረጋገጥን ድረስ ከአደጉ አገራት የመማራችን ሂደት ቀጣይነት ይኖረዋል። በእርግጥ አድገንም ቢሆን እስከጠቀመ ድረስ ከሌላ መማሩ አይጎዳም። ኢትዮጵያ የ3 ሺህ ዓመታት ታሪክ እንዲሁም ረዥም የመንግሥት አስተዳደር ታሪክ ያላት መሆኑን የራሳችንም የውጭ መጻህፍት ድርሳናትም ያስረዳሉ። በአንጻሩ ድህነትና ኋላቀርነትም ለበርካታ ዘመናት አሁንም ድረስ እግር በእግር እየተከተለ የዛሬይቷን ኢትዮጵያ መፈተኑ አልቀረም። በተለይም ለዘመናት የዘለቁ የጦርነት ጊዜያትና በፖለቲካው መስክ ያሉ ስንጥቃቶች ዛሬም ድረስ ተጽዕኗቸው እጅግ የጎላ ነው። ምንም እንኳን እንዲህ ያሉ የተዋረሱ ችግሮች አሉታዊ ተጽዕኗቸው በሁሉም ዘርፎች ላይ ቢሆንም በተለይም በምጣኔ ሀብት ረገድ አገሪቱ ፈቅ እንዳትል አድርጓታል።

ያለፈው ታሪካችን አሁን ላይ ተጽዕኖው እንዳለ ሆኖ መጪው ጊዜ በሕይወታችን የሚያጓጓና ትልቁን ሥፍራ መያዙ አይቀሬ መሆኑን በመረዳት የተሻለች ኢትዮጵያን በኅብረት ለመገንባት ቆርጦ መነሳት ያሻል። በዚህ ረገድ በተለይም የቻይና ዕድገት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ምንም እንኳን የተከተሉትን የኢኮኖሚ ሞዴል ጠቅልሎ ገቢራዊ ማድረግ ባይቻልም ቢያንስ ለበርካታ አገራት ሊሰራ የሚችለውንና የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ላይ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኘውን በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። በተለይም ግብርናውን ማዘመንና የኢንዱስትሪ ልማትን ሊያስፋፉ የሚችሉ እንደ ጥቃቅንና አነስተኛ የመሰሉ ተቋማት በስፋት ማደራጀትና ወደ ተግባር ማስገባት ያስፈልጋል። በውስጣቸውም  የሕዝቡን ህይወት ሊቀይሩ የሚችሉ ተጨባጭ የፈጠራ ሥራዎች እንዲስፋፉ የሚያስችሉ በፖሊሲ የተደገፉ ሥራዎችን መሥራት ግድ ይላል።  

ጎን ለጎንም ሕዝቡን በማንቃትና በማደራጀት ለአንድ አገራዊ ዓላማ እንዲሰለፍ ማድረግ ሌላው ከቻይና የምንማረው ጉዳይ ነው እላለሁ። አሁን ላይ በተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳዎች ተጠምዶ ቀን ከሌት የሚያሰላስለውን ወጣት ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር የሚያስችሉ  ሥራዎች መሥራት ያሻል እላለሁ። በዚህ ላይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የአሁኗና የወደፊቷ ኢትዮጵያ የምትገዳቸው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የወል ኃላፊነት መሆኑንም ልብ ይሏል። አብዝተው ስለ ራሳቸውና ስለቤተሰባቸው ከፍ ሲልም ማኅበረሰብንና አገራቸውን በሚጠቅሙና የጋራ ረብ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ባለ ራዕይ ወጣቶች ያስፈልጉናል። በበርካታ ጉዳዮች ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም ጽሑፌን እዚህ ጋር ገትቼ ኢትዮጵያም እንደ እስያ ቻይና አድጋ ተመንድጋ እንድናያት እወዳለሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም