በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለ ሀብቶችና ተቋማት በቴክኖሎጂው ሥራ ፈጠራ ላይ የተሠማሩ ወጣቶችን እንዲደግፉ ተጠየቀ

189

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለ ሀብቶችና ተቋማት በቴክኖሎጂው ሥራ ፈጠራ ላይ የተሠማሩ ወጣቶች አቅም እንዲጎለብትና ስራቸውን ወደ ገበያ ለማድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ጋር በመሆን በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች የስራ ፈጠራ እድሎችና ተግዳሮት ላይ ያተኮረ ውይይት እያካሄደ ነው።


በተጨማሪም በመርሐግብሩ በ2014 ዓ/ም የክረምት መርሃ ግብር ፕሮግራም (Summer Camp) ለአንድ ወር ያህል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዮኒቨርስቲ ሲሰለጥኑ የቆዩ ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶች የሰሯቸውን የፈጠራ ሥራዎች ለእይታ አቅርበዋል።


የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ኢትዮጵያ የ10 ዓመት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዕቅድ በማውጣትና ቀድመው የነበሩትን በመከለስ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል።


በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ባለ ልዮ ተሰጥኦ የሆኑ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ስልጠናና ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ተቋም በማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


ተግባሩን ከመንግሥት ጎን በመሆን ተቋማት እና ባለ ሀብቶችም ሊያግዙ እንደሚገባ አመልክተዋል።


የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ ኢመደአ በክረምት መርሃ ግብር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር 60 የሚሆኑ ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶችን ማሰልጠኑን ገልጸዋል፡፡


120 የሚጠጉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶች በታለንት ማዕከሉ ውስጥ አቅፎ ድጋፍ እያደረገ እና ወደ ገበያ የሚገቡበትን ሁኔታዎች እያመቻቸ እንደሚገኝ ነው ያነሱት፡፡


መድረኩ የወጣቶቹን የስራ ፈጠራ ከማቅረብ ባሻገር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።


በዚህም በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለ ሀብቶችና ተቋማት በቴክኖሎጂ ሥራ ፈጠራ ላይ የተሠማሩ ወጣቶች አቅም እንዲጎለብትና ስራቸውን ወደ ገበያ እንዲደርስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።


በመድረኩ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ባለ ሀብቶችና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም