የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥትና የግል አጋርነት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ

162

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015  የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማጠናከር ያግዛል በሚል የተዘጋጀው የመንግሥትና የግል አጋርነት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው አዋጁ በግልና በመንግሥት ጥምረት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት የሚጠቅም መሆኑን በመገንዘብ አፅድቆታል።

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ፤ የመንግሥትና የግል አጋርነት አሰራር የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማገዝ በመንግሥትና በግል ጥምረት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።

በዚህም የሕዝብ አገልግሎት መስጫ መሰረተ-ልማቶችን ጥራትና ደረጃ ለማስፋፋት አሰራሩን ተግባራዊ በማድረግ በኩል እስካሁን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እንዲረዳ አዋጁን ማሻሻል እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

ለአገር ምጣኔ ሃብት ዕድገት የግሉ ዘርፍ ያለውን አስተዋጽኦ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማንሳት አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

በአዋጁ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያደረገው ምክር ቤቱም የአዋጁን አስፈላጊነት በመረዳት በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል።

የብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ብዙ ሥራቸው ከባንክ ጋር የሚገናኝ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ የባንክ ሥራን ተክተው የሚሰሩ ባለመሆናቸው አዋጁን ማሻሻል ማስፈለጉን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ አዳዲስ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ምደባን አስመልክቶ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይም ተወያይቶ ምደባውን አፅድቋል።

በዚህም መሰረት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ እንዲሁም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሃመድ አብዶ ሆነው እንዲያገለግሉ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አፅድቋል።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ብዛት 13 ሲሆን የእያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ብዛት ዝቅተኛው 19 ከፍተኛው ደግሞ 25 በመሆን ተደራጅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም