በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀመረ

145

ባህር ዳር፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዛሬ በዘመቻ መስጠት ተጀመረ።

በአማራ እና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር ዛሬ መስጠት በተጀመረው የኩፍኝ መከላከያ ዘመቻ ቁጥራቸው ከ3 ሚሊዮን 106 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሕጻናት እንደሚከተቡ ተገልጿል።

በአማራ ክልል ደረጃ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ዛሬ የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት የተጀመረው በባህር ዳር ከተማ ሹም አቦ ጤና ጣቢያ ነው።

የክልሉ ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ በክትባቱ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት ክትባቱ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል።

"በእነዚህ ቀናት በክልሉ ከ3 ሚሊዮን የሚበልጡ ሕጻናት ክትባቱን እንደሚወስዱ ጠቁመው፣ ለክትባቱ ከ4 ሺህ 100 በላይ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል" ብለዋል።

ክትባቱ ዕድሜያቸው ከ9 ወር እስከ 5 ዓመት ዓመት ለሆነና ከዚህ በፊት ለተከተቡም ሆነ ላልተከተቡ ሁሉም ሕጻናት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት በክልሉ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታና በሌሎች ምክንያቶች ተገቢ ትኩረት ባለመሰጠቱ ዘንድሮ የኩፍኝ በሽታ በክልሉ 9  ዞኖች ተስፋፍቷል።

በመሆኑም ሁሉም ወላጆች ከዚህ በፊት የተከተቡም ሆነ ያልተከተቡ ህፃናት ልጆችን ወደ ክትባት መስጫ ጣቢያዎች በማምጣት እንዲያስከትቡም ጥሪ አቅርበዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት የአጣዳፊና የምግብ ዕጥረት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ እና የሆድ ጥገኛ ትላትል መድኃኒት ዕደላና ሌሎች ተግባራትም ከክትባት ዘመቻው ጋር በቅንጅት ይሰጣሉ።

በተመሳሳይ በሐረሪ ክልል ከ36ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀምሯል።

ክትባቱም በክልሉ ኤረር ወረዳ ሃዋይ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሁሮ ሳተላይት ትምህርት ቤት ዛሬ መስጠት የተጀመረው የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈቲህ መሃዲ  በተገኙበት  ነው።

አቶ ፈቲህ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ሕጻናት ክትባቱን ይወስዳሉ።

በኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ወቅት የአንጀት ጥገኛ ትላትል እና ሌሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች በተጨማሪነት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

ክትባቶቹና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶቹ በጤና ኬላ፣ ጤና ጣቢያ፣ በሆስፒታሎች  እና ለዘመቻው በተዘጋጁ ጊዜያዊ ጣቢያዎች እንደሚሰጡም አቶ ፈቲህ ገልጽዋል።

ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት የሚዘልቀው የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በድሬዳዋ አስተዳደርም ዛሬ ተጀምሯል።

በድሬዳዋ በኢንዱስትሪ መንደር በሚገኘው አዲሱ ጤና ጣቢያ ተገኝተው ክትባቱን ያስጀመሩት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከዲር ጁሃር እና የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ናቸው።

ከንቲባ ከዲር ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ወላጆች  ዕድሜያቸው ከ9 ወራት እስከ 5 ዓመት የሆናቸው ህፃናትን በማስከተብ ጤናማና አምራች ዜጋ የማፍራቱን ሂደት ማሳካት ይጠበቅባቸዋል።

የድሬደዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው፣ "ዛሬ በተጀመረው እና ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት በሚሰጠው ክትባት 70 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሕጻናት ይከተባሉ" ብለዋል።

ወላጆች በየአቅራቢያቸው በተቋቋሙት ጊዚያዊ ከትባት መስጫ ማዕከላት እና ጤና ጣቢያዎች ህፃናትን ወስደው ማስከተብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት ለዘመቻው መሳካት አስፈላጊው የሕክምና እና የባለሙያዎች ቡድን ተደራጅቶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን አስፈላጊ የቅስቀሳ ስራም ተሰርቷል።

የጤና ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም አማካሪ አቶ ስለሺ ሰሎሞን በበኩላቸው፣ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ሽፋንን እንደ ሀገር 95 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በጦርነቱ የጤናው ዘርፍ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በመላ ሀገሪቱ መጀመሩን አመልክተዋል።

በዘመቻው እንደሀገር ከ15 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚበልጡ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የክትባቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

"ሕብረተሰቡ ሳይዘናጋ ልጆቹን በማስከተብ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።

ለአስር ተከታታይ ቀናት በዘመቻ በሚሰጠው የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ወላጆች ህጻናትን ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ጥሪ ቀርቧል።

የኩፍኛ በሽታ በቫይረስ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን በተለይ ሕጻናትን በቀላሉ ለጉዳት የሚዳርግ በሽታ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም