የኢትዮጵያና የሕንድ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች እየተጠናከረ ነው

182

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳሰ 13/2015 የኢትዮጵያና የሕንድ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች እየተጠናከረ መምጣቱን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያና ሕንድ ለሺህ ዓመታት የዘለቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከንግድ ባለፈ በባህልም ጭምር የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው ግንኙነቱ አሁን ላይ በተለያዩ መስኮች ላይ መጠናከሩን ነው የጠቆሙት።

በተለይም ደግሞ ሕንድ ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1947 ጀምሮ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ስትራቴጂካዊ መልክ እየያዘ መምጣቱን አስረድተዋል።

ሕንድ በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራዎች ጉልህ ተሳትፎ እንዳላትም ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም በትምህርት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ነው ያሉት፡፡

ይህንንም ተከትሎ፤ አሁን ላይ የአገራቱ አዳዲስ የግንኙነት አድማሶችን በማስፋት ያላቸውን ወዳጅነት እያጠናከሩ መምጣታቸውንም ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

ሕንድ በኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ኢትዮጵያ በራሷ መፍታት ትችላለች የሚል በመርህ ላይ የተመረኮዘ አቋም ስታራምድ መቆየቷንም ነው ያነሱት።

ሕንድ የያዘችው አቋም "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" ከሚለው መርህ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ጠቁመው አሁንም ሕንድ ይህንን አቋሟን እንደምታስቀጥል ገልጸዋል።

በዚህ አውድ ሕንድ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በመንግሥትና በሕወሃት መካከል የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት የሚበረታታና አገራቸው በአዎንታ እንደምትመለከተው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሕንድ ካላቸው ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተጓዳኝ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ያሏቸውን ትበብርና ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

አሁን ላይ ሕንድ የቡድን 20 አገራት ወቅታዊ ፕሬዝዳንት መሆኗን ገልጸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ድምጽ እንዲሰማ ትሰራለች ብለዋል።

በሌላ በኩል በሁለቱ አገራት መካከል ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነትም የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያና የሕንድ ግንኙነት 2 ሺህ ዓመታት እንዳስቆጠረ የታሪክ ድርሳናት የሚጠቁሙ ሲሆን፤ የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተው ከዛሬ 75 ዓመታት በፊት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም