የፖሊስና ህዝቡን ትብብርና በጋራ መስራት የሚያጠናክር አገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድን ተመሰረተ

161

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 የፖሊስና ህዝቡን ትብብርና በጋራ መስራት የሚያጠናክር አገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድን በይፋ ተመሰረተ።

አገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ከመንግስት አካላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ያሉበት ሲሆን የፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማሳለጥ የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከሲቪል ማህበራትና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላትን ያካተተ መሆኑም ታውቋል።

አገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል በሰብሳቢነት የሚመሩት ሲሆን በፖሊስና ህብረተሰቡ ዘንድ ትብብርና አብሮነትን ማጠናከር እንዲሁም የፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑ ተመልክቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ በይፋ መመስረቱን በዛሬው እለት አብስረዋል።

አደረጃጀቱ ወንጀልንና የወንጀል ስጋቶችን በመቀነስ ሂደት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይ የወንጀል ስጋትን ለመቀነስና ቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም በማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግ መሰረተ-ሃሳብ የሆነውን "ፖሊስ የህዝብ፤ ህዝብ ደግሞ የፖሊስ" መሆኑን በተግባር የሚያመላክትና የሚያጠናክር አሰራር መፍጠር ያስችላል ተብሏል።

በተጨማሪም አገር በቀል ማህበራዊ ሀብቶች፣ እሴቶች እና ባህሎችን ከፖሊሳዊ ስራ ጋር በማስተሳሰር የህብረተሰቡን የህግ ማስከበርና በሰላም የመኖር ዋስትና በመስጠት የጸና የሰላም ባህል ለመገንባትም ጭምር መሆኑ ተመላክቷል።

ፖሊስ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ መረጃዎች፣ አቅጣጫዎችና መፍትሔዎችን በጋራ ማስቀመጥና ሌሎችንም ዓላማ መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ተብራርቷል።

አገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በክልሎች ደረጃ ተቋቁሞ ውጤት ማስገኘቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም