ፍላጎትን መሰረተ ያደረገ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ቀጥታ የማድረስ ስራ እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት

215

አዳማ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 ፍላጎትን መሰረተ ያደረገ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ቀጥታ የማድረስ ስራ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ከሁሉም ቅርንጫፎችና የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር የባለፉት አምስት ወራት የመድህኒትና ህክምና መሳሪያዎች ስርጭት አፈፃፀም እየገመገመ ይግኛል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት አገልግሎቱ በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የህክምና መሳሪያዎችና የመድኃኒት አቅርቦት ተግዳሮቶች ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ''የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሻሻል ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የአቅርቦት ስርዓት እየዘረጋን ነው'' ብለዋል።

በአቅርቦቱ ላይ ትልቁ ማነቆ የሆነው የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች መዳከም፣ በሀገሪቷ የነበረው የፀጥታ ችግርና በጤና ተቋማት ላይ ያለው የአቅርቦትና የፍላጎት ያለመጣጣም መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በቀጣይ የግዥ ስርዓት ማዘመን፣ የመድኃኒትና ህክምና መሳሪያዎች ቆጠራ ማካሄድ፣ ብልሹ አሰራሮችን የማስተካከል፣ የመድኃኒት ስርጭቱን ቀጥታ ለጤና ተቋማት ማድረስ ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ወራት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ግዥ ፈጽሞ ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

የ2015 ዓ.ም የመሰረታዊ መድኃኒቶችን ጨምሮ የህፃናት ክትባት፣ የኤች አይቪ ኤድስ፣ የቲቢና ሌሎች መድኃኒቶች ክምችት 85 በመቶ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት 17 ቢሊዮን ብር የመድኃኒትና የህክምና መሰሪያዎች ግዥና 42.9 ቢሊዮን ብር ዋጋ የነበራቸው የህክምና ግብአቶች ስርጭት መከናወኑንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም