ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስተዋወቅና ለጎብኚዎች ክፍት ለማድርግ እየተሰራ ነው - የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት

81

ጭሮ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስተዋወቅና ለጎብኚዎች ክፍት ለማድርግ እንደሚሰራ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዞኑ በርካታ ለቱሪስት መስህብነትና መዳረሻነት ሊውሉ የሚችሉ ጥንታዊ ቅርሶችና የተፈጥሮ ጸጋዎች መኖራቸውን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳኒ ረሺድ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ሊጎበኙና በሀገር ቅርስ ሀብትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ከ15 በላይ የተለያዩ ጥንታዊ ዋሻዎች አሉ።

በአንጫር፣ ዳሮለቡ፣ ሀብሮ፣ ዶባና ሌሎች ወረዳዎች ጥንዊ ዋሻዎቹ የሚገኙባቸው የዞኑ ወረዳዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፡፡

በዞኑ ጥብቅ ደን ተብለው የተከለሉ እንደ 'ጋራ ሙክታር'፣ 'ጋራ ጀሎ'፣ 'ጋራ ሀደስ'፣ 'ጋራ ገዳም' የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን የጠበቁ ደኖች መኖራቸውንም አክለዋል፡፡

በዶባ ወረዳ የሚገኘውና ለኢኮቱሪዝም መስህብነት እያገለገለ የሚገኘው የጨርጨር ሀይቅም ትልቁ የዞኑ የመስህብ ስፍራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በ16ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፋን ኦሮሞ የታተመ መፅሐፍ በዶባ ወረዳ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

እነዚህን የመስህብ ስፍራዎች በተሻለ መልኩ ለማስተዋወቅና ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ጅምር እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል።

የዞኑ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶች በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በቅርሶች ላይ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህም አልፎ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በተመተባበር የመዳረሻ ልማትና መሰረተ-ልማት ዝርጋታ ላይ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም