ቅርሶችን አልምቶ በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኝውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

197

ዲላ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን አልምቶ በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኝውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሰልጣን አስታወቀ።

የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር የጉብኝትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በመድረኩ እንዳሉት ኢትዮጵያ የረዥም ዓመታት ታሪክና የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ናት።

ቅርስ የማንነትና የወንድማማችነት ምልክት ከመሆኑ ባለፈ የኢኮኖሚ ጠቀሜታውን ለማሳደግ በዓለም ደረጃ የማስተዋወቅና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

"ይሁንና ቅርስን በማልማቱ በመንከባከቡና በማስተዋወቁ በኩል ውስንነቶች በመኖራቸው ከዘርፉ ማግኘት የሚገባንን ያህል ጥቅም አላገኘንም" ብለዋል።

"የቅርስ ተንከባካቢና ጠባቂ ማህበረሰቡ ነው" ያሉት ሃላፊው፤ ቅርሶቹ ዘንድ ሊያደርሱ የሚችሉ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት፣ ያሉትን በማልማትና በማስተዋወቅ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የቅርሶች ዋጋና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በኩል የሚዲያው ድርሻ የጎላ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ቀድሞ ከተመዘገቡት በተጨማሪ የሀገሪቱን ቅርሶች በዩኔስኮ በማስመዝገብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

የጌዴኦ ህዝብ በአካባቢ ጥበቃ ባህሉ ደንና አካባቢን እንደ ልጁ በመንከባከብ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ባህላዊ እውቀት ያለው ህዝብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጌዴኦ መልክዓ ምድር በርካታ ገጽታ እንዳለው ጠቁመው በተለይም ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ትክል ድንጋዮችና የድንጋይ ላይ ጽሑፍች በአፍሪካ ደረጃ ተጠቃሽ የሚሆኑ ትልቅ የቱሪዝም ሃብቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ይህንንም በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የወረቀት ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ምዕራፎችን በማለፍ ምዝገባውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

"የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ህዝቡ ለዘመናት አካባቢን በመጠበቅ ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር ምላሽ የሰጠበት ሀገር በቀል እውቀት ነው" ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።

የጌዴኦ አባቶች ለዘመናት ተንከባክበው የያዙትን ጥምር ግብርናና የትክል ድንጋዮች የመሳሰሉትን የቅርስ ሃብቶች ለትውልድ ማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ሃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበል።

ለሀገር እድገትና ታሪክ የቅርስ ጥበቃ መሰረት መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዝናቡ፤ የጌዴኦን ባህላዊ መልክዓ ምድር በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ጠቄሜታውን በማሳደግ በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይ መገናኛ ብዙሃን ግንባር ቀደም ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ የጌዴኦ ባህል እና መልክዓ ምድር ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

መድረኩን ተከትሎ የመልክዓ ምድር ጉብኝት እንደሚካሄድ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም