በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ ተቋቋመ

203

ጎንደር (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የእሳት አደጋ በዘመናዊ ዘዴ ለመቆጣጠር የሚያስችል የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ።

የፓርኩ ጽህፈት ቤት እንደገለጸው ብርጌዱ የተቋቋመው በዘመናዊ የእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዘዴዎች ላይ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር 200 ባለሙያዎችን በማሰልጠን ነው።

የፓርኩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የዓለም ቅርስ በሆነው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ተከስቷል።

ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የእሳት አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል የብርጌዱ መቋቋም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት ብርጌዱ በፓርኩ አዋስኝ በሆኑ 6 ወረዳዎች ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

የብርጌዱ አባላት ከፓርኩ እስካውቶች እና ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተውጣጡ መሆናቸውንና አንስተው በፓርኩ ውስጥ እሳት ቢከሰት እንኳ ብርቅዬ በሆኑት ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ሌሎች ብዝሃ ህይወቶች ላይ ጉዳት ሳይደርስ ፈጥኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ብርጌዱ ሃላፊነት በሚገባ እንዲወጣም ዘመናዊ የእሳት መከላከያ አልባሳት፣ ጫማዎች እና ሄልሜቶች እንዲሁም የእሳት ማጥፊያ ኬሚካሎች እና ሌሎች ቁሶች እንዲሟሉለት መደረጉንም አስረድተዋል።

"በቀላሉ በእጅ የሚንቀሳቀሱ የእሳት ማጥፊያና የኬሚካል መርጫ መሳሪያዎች እንዲሁም ቃጠሎ እንዳይዛመት መከላከል የሚያስችሉ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ብርጌዱ ታጥቋል" ብለዋል።

የእሳት አደጋ ብርጌዱ የቃጠሎ ስጋት ባላበቸው የፓርኩ የተለያዩ አካባቢዎች የ24 ሰዓት የቅኝትና የአሰሳ ሥራ እንዲያከናውን ተልእኮ እንደተሰጠውም አስገንዝበዋል።

"አፍሪካን ዋይልድ ፋውንዴሽን" የተባለው ድርጅት ለፓርኩ የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በማስታጠቅና በስልጠና ድጋፍ ማድረጉንም አስረድተዋል።

"የፓርኩን ደህንነት በመጠበቅ በኩል 7ሺህ የሚሆኑ አባላቱ ከፓርኩ ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ ናቸው" ያሉት ደግሞ የደባርቅ ከተማ የኢኮ ቱሪዝም ዩኔየን ሊቀ-መንበር ሞገስ አየነው ናቸው፡፡

ቀደም ሲል በፓርኩ ክልል ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ አባላቱ እገዛ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ በተቋቋመው የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ ውስጥም አባላቱ መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በ2011 ዓ.ም እና በ2013 ዓ.ም ተከስቶ በነበረ የእሳት ቃጠሎ በ1 ሺህ ሄክታር የጓሳ ሣርና የቁጥቋጦ ዛፎች ላይ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም