የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢዜአ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሹመትን አፀደቀ

256

አዲስ አበባ  (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሹመትን በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቀረቡ የኢዜአ ዕጩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት ሹመትን መርምሮ አፅድቋል።

 የቦርድ አባላት

ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ -       የቦርዱ ሰብሳቢ

አቶ መሃመድራፊዕ አባራያ-  አባል

አቶ ሙሳ አህመድ -                አባል

ወይዘሮ ሚሊዮን ተረፈ-      አባል

ወይዘሮ ሁሪያ አሊ-             አባል

ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ-  አባል    ሆነው ተሹመዋል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ የሹመቱን የውሳኔ ሃሳብና የተሿሚዎችን የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ አቅርበዋል።

የቦርድ አባላቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዓላማና ተልዕኮ ተገንዝበው አመራር መስጠት የሚያስችል እውቀትና ልምድ እንዲሁም ሌሎች መስፈርቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መመረጣቸውን ገልጸዋል።

የቦርድ አባላቱ ተቋሙ ሕብረ-ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በማጠናከር ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ አቅጣጫ ማመላከት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የቦርድ አባላቱ  ከትምህርት ዝግጅታቸው፣ ከሥራ ልምዳቸውና የሚዲያ ዘርፉን የሚያውቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ  ተቋሙ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ የቀረቡትን ዕጩ የቦርድ አባላት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ተልዕኮ በመገንዘብ አመራር መስጠት ይችላሉ በማለት በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ የቦርድ አባላቱ ኢዜአ በሥራው ከዓለም አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አዲስ የተሾሙ የቦርድ አባላት በምክር ቤት ቀርበው ቃለ-መሃላ በመፈጸም ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 1115/2011 መሠረት የተቋሙ የቦርድ አባላት አግባብነት ካላቸው ተቋማትና ከልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚመረጡ  ይደነግጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም