የዜጎችንና የአገር ደህንነትን በብቃት የማስጠበቅ አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ነው

96
አዲስ አበባ መስከረም 20/2011 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገለልተኝነትን ባረጋገጠ መንገድ የዜጎችንና የአገር ደህንነትን በብቃት የማስጠበቅ አቅምን ለመፍጠር የሚያስችል የለውጥ ማሻሻያ ስራዎች እየተካሄዱ እንደሆነ ተገለፀ። ይህ የተገለፀው “የኢትዮጵያ የደህንነት ዘርፍ ሪፎርም ፍላጎቶች፣ ልምዶችና የወደፊት ራዕይ”  በሚል ትናንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ ነው። በዚሁ ወቅት የመከላከያ ሰራዊት እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊዎች እየተካሄደ ባለው በተቋማቱ የለውጥ ማሻሻያ ስራዎች ዙሪያ ለሲምፖዚየሙ ታዳሚያን ማብራሪያ ሰጥተዋል። ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎችም በማሻሻያው ላይ ያተኮሩ የመወያያ ፅሑፎችን አቅርበዋል። በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የክንፈ ብሔራዊ ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አሰፋ እንደገለፁት፤ የዜጎችና የአገር ደህንነትን የመጠበቅ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል የለውጥ ማሻሻያ ስራ እየተሰራ ይገኛል። የደህንነት መስሪያ ቤቱን የፖለቲካ ገለልተኝት፣ በህግ መወሰንና በህግ የበላይነት መገዛትን ማረጋገጥ የማሻሻያው ዓላማ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህ መሰረት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የስነ ምግባር አሰራርና መመሪያዎችን ጨምሮ የቅሬታ አፈታት፣ የውስጥ ቁጥጥርና ክትትል ደንቦች የማሻሻል ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አቶ መኮንን ጠቁመዋል። ማሻሻያው ከደህንነት መስሪያ ቤቱ ባሻገር የፍትህ ተቋማት፣ የግልና የንግድ ጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ  አካላት ተቀናጅተው በጋራ ለአገርና ለህዝብ ደህንነት የሚሰሩበትን ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቅሷል። አቶ መኮንን እንዳሉት፤ የማሻሻያ ተግባሩ ያስፈለገው በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ የሚጠይቀውን ቁመና ከመፍጠር ባሻገር፤  በአገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ  ሁኔታዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ተለዋዋጭ ስጋቶችን ለመከላከል ጭምር ነው። ''ማሻሻያው የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የደህንነት ሥራን ከፖለቲካ ተፅእኖ እንዲላቀቅ ለማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ በመሆኑም ነው'' ሲሉ አቶ መኮነን ተናግረዋል። ዘመን ተሻጋሪ ተቋምና እሴት ለመፍጠር፣ የህዝብ ኃብት በአግባቡ ለመጠቀምና በሙያተኞች የሚመራ የደህንነት መስርያ ቤት እንዲሆን ለማስቻል የማሻሻያ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል። በአገር መከላከያ ሰራዊት እየተካሄደ ስላለው ማሻሻያ ማብራሪያ የሰጡት ሌተናል ጀኔራል ሀሰን ኢብራሂም በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያለውን የመከላከያ ሰራዊት ማቋቋሚያ አዋጅ ጨምሮ መላው ሰራዊቱን ለማዘመን የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። "2011 ዓም  የሪፎርም ዓመት እንዲሆን ተሰይሟል” ያሉት ሌተናል ጄኔራል ሀሰን የሰራዊቱ አመራርን ተጠያቂነት ማረጋገጥና አቅም ማጎልበት የማሻሻያ ስራው አካል መሆኑን ገልጸዋል። እስካሁን ባለው አሰራር በተቋሙ የዘመቻና የሀብት ጉዳዮችን በብቸኝነት የሚወስነው የአዛዦች ካውንስል እንደሆነ አስታውሰው አሁን እየተካሄደ ባለው ማሻሻያ ካውንስሉ ለሁለት የሚከፈልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። በዚህም የሀገር መከላከያ መስሪያ ቤት ሲቪል የሥራ ክፍሎች የተካተቱበት የሀብት ጉዳዮችን የሚወስን የመከላከያ ካውንስል እንዲኖር የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል። የማሻሻያው ዓላማ በተቋሙ ውስጥ  በሚወሰዱ እርምጃዎች ጠንካራ የሆነ የተጠያቂነትና ግልፅነት ስርዓትን ለመፍጠር መሆኑን አብራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በክልልና በፌዴራል የፀጥታ አካላት መካከል የሚስተዋለውን የመደጋገፍ እጥረት እና የስራ ድርሻ መደበላለቅ ለማጥራት ማሻሻያው ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሰራዊት ከተልእኮው ውጭ በፖሊሶችና መደበኛ ህግ አስከባሪዎች ሊከናወኑ የሚገባቸውን መደበኛ የህግ ማስከበር ሥራዎችን ጭምር እንደሚሰራ የጠቀሱት ሌተናል ጀኔራል ሀሰን የመደበኛ ህግ አስከባሪዎችን አቅም በማሳደግ ይህንን ለመፍታት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ሰራዊቱ ጠንካራ ህዝባዊነት እንዳለው የገለፁት ሌቴናል ጀኔራል ሀሰን ይህንን በይበልጥ ለማጎልበት ይቻል ዘንድ ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ማስፋፋት የማሻሻያው አካል ተደርጎ እንደሚሰራበት አመልክተዋል። ''በዚህ መሰረት የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት በየወሩ መግለጫዎችን ይሰጣል፤ የተለያዩ ኮንፈረንሶችን እንዲያዘጋጅም ስርዓት ይበጃል'' በማለት  ገልፀዋል። በሲምፖዚየሙ የመወያያ ፅሑፍ ያቀረቡት የቀድሞው ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ በበኩላቸው በደህንነት መስክ የተጀመረውን የማሻሻያ ስራ በማድነቅ ሪፎርሙ ከሁሉም የደህንነት ዘርፍ ጋር የተቀናጀና አገራዊ ደህንነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን መክረዋል። ''የኢትዮጵያ የደህንነት ፖሊሲም መሻሻል አለበት'' ያሉት ሌተናል ጀኔራል ጻድቃን የብሔራዊ ደህንነት ካውንስልም ይበልጥ መጠናከር እንደሚገባው ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሙያተኞች የተጠናከረና የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችንና ውሳኔዎችን የሚያቀርብ የተደራጀ የብሔራዊ ደህንነት ካውንስል ፅህፈት ቤት እንዲመሰረት ሌተናል ጀኔራል ጻድቃን መክረዋል። በሲምፖዚየሙ የተነሱ ምክረ ሀሳቦች የደህንነት ዘርፍ ማሻሻያውን ለማጠናከር በግብአትነት እንደሚወሰዱ በውይይቱ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት የአገሪቱን የደህንነት ተቋማት አሰራር ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ መካሄዱ የዜጎችን የባለቤትነት ስሜትና እምነት እንዲያገኝ የሚያደርግ በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባው ተሳታፊዎቹ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም