ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶችን እንደ ዕድል ማሰስ

244

(በጌታቸው ያለው)

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አፍሪካ የዓለም የኢኮኖሚ እና የጂኦፖለቲካ እይታ በእጀጉ ያረፈባት አሕጉር ሆናለች። ከታኅሣሥ 4 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በዋሽንግተን የተካሄደው ሁለተኛው የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔም በአፍሪካ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ፍላጎት የቱን ያህል እያደገ መምጣቱን ያሳያል።

በአፍሪካ የተጽዕኖ ክልል

“የተጽዕኖ ክልል” ወይም Sphere of Influence (SoI) የሚለው ቃል በዓለም የፖለቲካ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው እንደ ጎርጎረሳውያኑ የጊዜ ቀመር በ1884-1885 በተካሄደው የበርሊን ኮንፈረንስ እንደሆነ ድርሳናት ያስረዳሉ። በዘመነ ቅኝ ግዛት የጀመረው በአገራት ላይ የተጽዕኖ ክልል የመፍጠር አባዜ ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍሎ በቆየው ቀዝቃዘው ጦርነትም ቀጥሎ ተስተውሏል።

መልክና አቀራረቡ ይለዋወጥ እንጂ አሁን ላይም የኃያላኑ የተጽዕኖ ክልል የመፍጠር እሳቤ የሚያባራ አልሆነም። የምሥራቅ አውሮፓ፣ ኢንዶ-ፓስፊክ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪካ አገራት ደግሞ የዚህ አባዜ ሰለባ ሆነው ቀጥለዋል።

ከአሃዳዊ ወደ አብዝሃ ዓለማዊ ሥርዓት (Uni-Polar to Multi-Polar) ለመሸጋገር በሚደረገው የኃያላን ብርቱ ፉክክር እንደ አፍሪካ ባሉ አገራት የተጽዕኖ ክልል የመፍጠር ፍጥጫው የተለየ መልክ እንዲይዝ አድርጎታል።

የምዕራቡም ሆኑ የምሥራቁ ኃያላን አገራት አፍሪካን በተጽዕኗቸው ሥር ለማስገባት ይበጀናል ያሉትን አካሄድ ሲከተሉና ሲተገብሩ ይስተዋላሉ። ከቻይና-አፍሪካ ትብብር መድረክ (FOCAC) እስከ ጃፓኑ የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት ኮንፈረንስ (TICAD) ከሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ እስከ የአፍሪካ-ቱርክ አጋርነት፣ ከአውሮፓ ኅብረት-የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ እስከ የአሜሪካ እና አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ስያሜያቸው የቱን ያህል ይለያይ እንጂ ግባቸው አንድና ያው ነው፤ በአፍሪካ የተጽዕኖ ክልል መፍጠር።

የመስኩ ተንታኞች እንደሚሉት አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመን በአፍሪካ ላይ የነበራት ተጽዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። ይህን የተገነዘበው የባይደን አስተዳደር 49 የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በዋሽንግተን ታላቅ በተባለለት ጉባዔ ላይ በመጋበዝ ለአፍሪካ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 55 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገባው።

ይህም በአሜሪካ እና አፍሪካ የትብብር ታሪክ ግዙፍ ገንዘብ ተብሎለታል። አሜሪካ በየዓመቱ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከምትስጠው ከ 8 ቢሊዮን ዶላር ያልበለጠ ድጋፍ ጋር ሲነፃጸር በእርግጥም ላቅ ያለ መጠን ነው። 

ጉባዔው አሜሪካ ለአፍሪካ ያላትን “ዘላቂ ቁርጠኝነት” እንደሚያሳይ የተነገረለት ሲሆን የአሜሪካ እና አፍሪካ ግንኙነት አስፈላጊነት እና በዓለም አቀፍ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ትብብርን ይጨምራል ተብሎለታል።

ይሁን እንጂ ጉባዔው የአሜሪካ እና የአፍሪካ ግንኙነት እየቀነሰ በመጣበት እና እንደ ቻይና፣ ሩሲያ እና ቱርክ ያሉ ተቀናቃኝ ሀገራት በአፍሪካ ላይ ሰፊ ተሳትፎ እያደረጉ ባለበት ወቅት መሆኑ አሜሪካንን ሥጋት ላይ የጣላት ይመስላል። አሜሪካ ለወትሮ ያለተቀናቃኝ በአፍሪካ የነበራት የተጽዕኖ ፈጣሪነት አሁን ላይ መሸርሸሩን ልብ ማለትም ጀምራለች። ለዚህ ነው የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ የባይደን አስተዳደር የፖሊሲ ማዘመን በሚምስል ዓይነት የአቀራረብ ለውጥ የተስተዋለበት።

አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ያላትን እይታ አለማዘመን የአፍሮ-አሜሪካ ትብብርን ያቀዛቀዘው ሲሆን በአሕጉሪቱ የተደማጭነት አቅሟንም እያሳጣት ይገኛል። አሜሪካ ለዘመናት (አሁንም ድረስ) አፍሪካን እንደ ሰብዓዊ ቀውሶች ቦታ እና በዓለም አቀፍ ኃይል መካከል ፉክክር ለመፍጠር እንደ ምቹ ምክንያት ነው የምትመለከታት።

በአንፃሩ ቻይና አፍሪካን ትብብርን መሰረት ያደረገ የልማት አጋርነት መፍጠሯ በምዕራባውያን ዘንድ በበጎ ሊታይ አልቻለም። ይልቁንም ቻይና ልዕለ ኃያል አገር ለመሆን የምታደርገውን ጂኦ-ስትራቴጂያዊ ጥረት አካል ነው ለሚለው ውንጀላ እንደ ማስረጃ ሲያቀርቡት ይታያሉ።

ይህን በማሳያነት እንመልከተው። የአሜሪካ ኢንተርፕራይዝ የህዝብ ፖሊሲ ጥናት ተቋም (AEI) መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ጊዜ ቻይና የአፍሪካ ግዙፍ የንግድ አጋር ከመሆን ባለፈ የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ሸሪክ ሆና ቀጥላለች። እኤአ አቆጣጠር ከ2005 አንስቶ ቻይና በአፍሪካ ያላት የኢንቨስትመንት እና የግንባታ አጠቃላይ የንግድ ዋጋም 2 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ መድረሱን ተቋሙ ይፋ አድርጓል።

ቻይና ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአህጉሪቱ ጋር እየጨመረ የመጣውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቷን እያሳደገች ነው። በ 2021 አጠቃላይ የሁለትዮሽ ንግዷ 254 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን ከቀደመው አንድ ዓመት 35 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በዚህም በአፍሪካ ትልቋ የንግድ ሸሪክ መሆን ችላለች። በአንፃሩ በ2021 የአሜሪካ-አፍሪካ ንግድ 64.34 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ከቻይና ጋር ሲነፃጸር ግን የብዙ እጥፍ ቅናሽ ይታይበታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአፍሪካውያን ልሂቃን የተለመደች አንድ የተለመደች አባባል አለች። "ቻይና በአፍሪካ ስትሆን ስለ ኢንቨስትመንት ይወራል፤ አሜሪካ በአፍሪካ ስትሆን ግን ስለ ቻይና ነው የሚወራው" የሚል አባባል። እቺ የለበጣ አባባል አሜሪካ በአፍሪካ ያላትን የንግድ እና የመሰረተ ልማት ተሳትፎ ከቻይና የቱን ያህል የራቀ እንደሆነ ነው የሚያሳየው።

ይህን ክፍተትና መበለጥ ማስተካከል የተሳናት አሜሪካ ግን ቻይና በአፍሪካ የምታደርገው የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የገንዘብ ድጋፍ “ወጥመድ” (Debt Trap) ማለትን መርጣለች። በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር ቺን ጋንግ ባለፈው ሣምንት በዋሽንግተን በተካሄደው የሴማፎር አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ "ቻይና ለአፍሪካ የምታደርገው ኢንቨስትመንት እና የገንዘብ ድጋፍ ወጥመድ አይደለም" ሲሉ ሞግተዋል። ያም ተባለ ይህ ግን ሁሉም አገራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የተጽዕኖ ክልል መፍጠርን ታሰቢ አድርገው እየሰሩ ስለመሆናቸው ለማንም የተሰወረ አይደለም።

የሃያላኑ የጂኦ-ፖለቲካ ፍትጊያ

ልዕለ ኃያላን የሆኑት አሜሪካ እና ቻይና ዓለም አቀፋዊ ጂኦ-ስትራቴጂያዊ ፍላጎታቸው አሁን ላይ እየጨመረ መጥቷል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባህር አካባቢዎች ደግሞ በአሜሪካ እና ቻይና ጉልህ የሆነ ጂኦ-ስትራቴጂካዊ እይታ ውስጥ ከገቡ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ አኳያ የአሜሪካ እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ እይታ እና ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በቅርብ መፈተሽ አገራዊ ሥጋት እና ዕድሎችን ለመዳሰስ ይረዳል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት አገር ተደርጋ ትወሰዳለች። ከኢትዮጵያ ባሻገርም የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር አካባቢ በአሜሪካ ስትራቴጂያዊ እመነጽር የሚታዩ ናቸው።

የፕሬዝዳንት ጆይ ባይደን የአሜሪካን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛን ለመሾም መወሰናቸው፣ የኢትዮጵያን ግጭት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ መጠነ ሰፊ ተሳትፎ መኖር፣ በቅርቡ መቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ የምድር ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲሰማራ መወሰኑ፣ የአሜሪካ ጦር በጅቡቲ መገኘቱ እና ሌሎች አስፈላጊ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች የቀጣይ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትክረትን ያመለክታሉ።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የምታደርገውን ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላቅ ያለ ግምት የሚሰጠው ነው። እ.ኤ.አ. በ 2021 የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ መጠን 2.66 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፣ ከዚህ ውስጥ ቻይና ወደ 370 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሸቀጦችን ከኢትዮጵያ ወደ አገሯ አስገብታለች።

በአሜሪካ የሠላም ኢንስቲትዩት (USIP) የአፍሪካ ማዕከል ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ጆሴፍ ሳንይ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ማዕከል (Hub) ነች። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ወደ 400 የሚጠጉ የቻይና የግንባታና የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶችም ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ለቻይና አፍሪካ ፖሊሲ ቁልፍ ስትራተጂካዊ አጋር ሆና የቀጠለች ሲሆን በአህጉሪቱ ካላት ትልቅ ጠቀሜታ እና ቦታ አንፃር የአፍሪካ መግቢያ ተደርጋ ተወስዳለች። የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም በሲኖ-አፍሪካ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን ማሳደግ ሌላው የቀጣናው ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ለዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ድጋፍ ትልቅ ማሳያ ነው።

የአሜሪካ እና የቻይና ጂኦ-ስትራቴጂያዊ ፍላጎቶች አንድ ነገር ሆኖ ጉዳዩ “የሁለት ዝሆኖች” የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍትጊያ ሆኖ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሥጋት ውስጥ እንዳትገባ በዚህ ረገድ ጂኦ­-ፖለቲካዊ ጫናን የመቋቋም አቅም መገንባት ያስፈልጋል። ከጂኦ-ፖለቲካ ጫና የሚመነጩ ሥጋቶችን ለመዳሰስ የሚያስችል በሰው ኃይል፣ በመዋቅር እና በቴክኖሎጂ ላይ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ማድረግ ይጠበቅባታል።

ኢትዮጵያና ጂኦ­-ፖለቲካዊ ዕድሎች

አሁን አሁን በአፍሪካ ቀንድ አገራት የዓለም አቀፉ የጂኦ-ፖለቲካ ፉክክር በስፋት እየታየ ይገኛል። ፉክክሩ የውክልና ግጭቶችን በመጥመቅ ለቀጣናዊ አለመረጋጋት መንስኤ እየሆነ ነው። በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር አካባቢ ላቅ ያለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላት ኢትዮጵያም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዚህ የፉክክር ተጽዕኖ ሥር መውደቋ አልቀረም። 

በአሜሪካ ኢንተርፕራይዝ ተቋም (American Enterprise Institute-AEI) ከፍተኛ ተንታኝ እና የአፍሪካ ቡድን መሪ የሆኑት ኤሚሊ ኤስቴል በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ላቅ ያለ ስለመሆኑን በአሜሪካ ምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ፊት ያቀረቡት ትንታኔ ያሳያል።

በተለይ ከአሜሪካ ብሔራዊ ፍላጎቶች አኳያ ኢትዮጵያ የደህንነት ቁልፍ አጋር መሆኗን ያሰምሩበታል። ያም ሆኖ በጂኦፖለቲካ ፉክክር እየተባባሰ የመጣው የአካባቢ እና ክልላዊ ግጭቶች ኢትዮጵያን የማተራመስ ሴራ ቀጣናዊ አለመረጋጋትን ያስከትላል የሚል ሥጋት አላቸው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ መድረክ ለሚደረገው የአዲስ ዘመን ፉክክር ሥጋትና ዕድሎችን በሚገባ አጢና ለአገራዊ ጥቅሟ ማዋል ይጠበቅባታል። የጂኦፖለቲካል ፉክክር እና ዓለም ቀፋዊ ተጽዕኖ በአገራዊ ሠላምና ደህነንት እንዲሁም በልማትና ዲፕሎማሲ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና ወደ ጥቅምና ዕድሎች መቀየር ያስፈልጋል።

በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደው የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ በዋናነት መነሻው የአሜሪካ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን አጋጣሚውን ወደ ብሔራዊ ጥቅሟ ለመለወጥ ያስቻላት ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ጉባዔው ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያረፈባትን ኢ-ምክንያታዊ የዲፕሎማሲ ጫና በሚገባ ለማስረዳት መልካም አጋጣሚን የፈጠረ መሆኑን ያነሳሉ። 

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ ከነበረው ግጭት በመውጣት ሠላምን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት የተካሄደው ጉባዔ አጋጣሚውን ለብሔራዊ ጥቅሞች መጠበቅ የፈጠረው መልካም ዕድል አለ ይላሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ የተመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ልዑክ በጂኦ­-ፖለቲካዊ ውጣ ውረድ ውስጥ ያሉ ዕድሎችን በማሰስ ጉባዔውን ለላቀ አገራዊ ፋይዳ ማዋል መቻሉ ከተገኙ ስኬቶች መገንዘብ ይቻላል። ከተገኙት ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች ባሻገር የዓለም ባንክ የሥራ አስፈፃሚ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለኢትዮጵያ የ745 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማጽደቁ በማሳየነት የሚነሳ ነው።

በተለይ በተሳሳተ መረጃ የተለያየ አቋም ይዘው የነበሩ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የአሜሪካ መንግሥት ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በአካል በማግኝት የኢትዮጵያን እውነታ ለማስረዳት የጉባዔውን አጋጣሚ ወደ አገራዊ ዕድል መለወጥ ተችሏል።

ከጉባዔው በተጓዳኝ በነበሩ የጎንዮሽ መድረኮችም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮችንና ስለተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለአሜሪካውያን ባለኃብቶች እና ኩባንያዎች ሰፊ ማብራሪያ መስጠት ተችሏል። በዚህም በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ሙዓለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ መልካም ምላሽ አሳይተዋል።

በአፍሪካ ስላለው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ዙሪያ በመክረው የቢዝነስ ፎረም ላይም አሜሪካ እና ኢትዮጵያን ከአፍሪካ የቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) በተጨማሪ በሌሎች የንግድ መስኮች አጋርነታቸውን መልስው እንዲያጠናክሩ ሀሳብ ማቅረብ ተችሏል።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ያደረገችው ተሳትፎ በብዙ መልኩ አትራፊ መሆን ችላለች። በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሥጋት እና ዕድሎችን በጥልቀት ገምግሞና ተንትኖ ጉባዔውን ወደ አገራዊ ፋይዳ መቀየር የቻለበት ዕድል ፈጥሯል።

ሥጋትን በንቃት ማሰስ መቻል ማለት በችግር ጊዜ መበልፀግ ወይም ሰለባ በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት የሚያመላክት በመሆኑ በቀጣይም በፖለቲካ ኢኮኖሚ እና በጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን ወቅታዊ እውነታዎችን በጥልቀት ተንትኖ በመረዳት ወደ ዕድሎች የመቀየር ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም