ኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙ ሴቶችን ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ገለጸ

203

ባህርዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 8 ቀን 2015 በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ሴቶች እራሳቸውን እንዲችሉ ለማቋቋም እየደገፈ መሆኑን የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ገለጸ።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከስዊድን መንግስት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከድርጅቱ ጋር በመተባበር በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙ 91 ወጣት ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ የልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ፤ ከቤተሰባቸው በተለያየ ምክንያት በመውጣት ለከፋ ችግር ተጋልጠው የሚገኙ ወጣት ሴቶች ብዙዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

እነዚህ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ሴቶችን በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በባህርዳር ከተማም 91 ወጣት ሴቶችን ለ5 ወራት የህይወት ክህሎት፣ የምግብ ዝግጅት፣ የሽመና፣ የፀጉር ስራና ሌሎች ሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ዛሬ ለምረቃ ማብቃቱን ጠቅሰዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ለማሰማራት ለእያንዳንዳቸው የሶስት ወራት የቤት ኪራይና በ25ሺህ ብር ወጪ የመስሪያ ቁሳቁስ ተገዝቶ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

ተመራቂዎችም በቆይታቸው ያገኙትን ሙያዊ ዕውቀትና የስራ ተነሳሽነት በመጠቀም ከነበሩበት አስከፊ ህይወት ራሳቸውን በማላቀቅ ቤተሰባቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ተግተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ድርጅቱ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከስዊድን መንግስት ባገኘው 59 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ በሚያካሂደው የሶስት ዓመት ፕሮጀክት የዛሬዎችን ጨምሮ እስካሁን በባህርዳር የሚገኙ 309 ወጣት ሴቶችን ራሳቸውን ማስቻሉ ተመልክቷል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የሻረግ ፋንታሁን በበኩላቸው ፤ ወጣት ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ወጥተው ለአስከፊ ህይወት ተጋልጠው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ ድርጅቱ አሰልጥኖ ወደ ስራ በማስገባት እያከናወነ ያለው ተግባር ለሌሎች አጋር ድርጅቶች አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል።

ከችግሩ ስፋት አንጻር በአንድ ድርጅት ይሄ ችግር የማይፈታ መሆኑን በመገንዘብ ሌሎች ድርጅቶች እንዲደግፉ አመልክተዋል።

የዕድሉ ተጠቃሚዎችም ጠንክረው ሰርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመጥቀም ባሻገር ለሌሎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ወጣት ማህሌት መዝገቡ ድርጅቱ ከነበርኩበት አስከፊ ህይወት በማውጣት የስነ ልቦናና የምግብ ዝግጅት ላይ አስተምሮኝ ለምረቃ በመብቃቴ በሰለጠንኩበት ሙያ ሰርቼ ራሴንና ቤተሰቤን ለመቀየር ተነሳሽነት ፈጥሮልኛል ብላለች።

ቀደም ሲል በድርጅቱ ስልጠና ወስዳ ወደ ስራ የገባቸው ወጣት መቅደስ አለለኝ በበኩሏ ለአምስት ዓመታት በሴተኛ አዳሪነት በሰራችባቸው ጊዘያት ለአስከፊ ህይወት ተዳርጋ መቆየቷን አስታውሳ፤ 

በተደረገላት ድጋፍ የራሷን ፀጉር ቤት ከፍታ ራሷንና ቤተሰቧን እያገዘች መሆኑን ተናግራለች።

ኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት በሀገሪቱ 25 ከተሞች በራሱና ከአጋሮች ጋር በመተባበር የተለያዩ የልማት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ድርጅቱ መሰል ችግር ላይ የነበሩ ሴቶችን አሰልጥኖ ሲያስመርቅ የአሁኑ ለ7ኛ ጊዜ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም