የኢሬቻ ባዛርና ኤክስፖ በዓሉን በዓለም ቅርስነት የማስመዝገብ ጥረቱን ያግዛል - አስተያየት ሰጪዎች

73
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 የኢሬቻ በዓል በየዓመቱ መስቀል ባለፈ በመጀመሪያው እሁድ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሀይቅ ሕዝብ በነቂስ በመውጣት በተለያዩ ትዕይንቶች በድምቀት የሚያከብረው ሲሆን በህብረተሰቡ ዘንድም በጉጉት ከሚጠበቁ የአደባባይ በዓላት አንዱ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና ከውጭ አገራት ጭምር በዓሉን ለማክበር በቢሾፍቱ ይሰባሰባሉ። ኢሬቻ ወርሃ ክረምት አልፎ ወደ ጸደይ ብርሃን የሚደረገው ሽግግር የሚከበርበትና ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው። የተጣሉ የሚታረቁበትና ቂም በቀል የሚሻርበት፤ እንዲሁም ፍቅር የሚሰበክበትና አንድነት የሚጎላበት መሆኑም የበዓሉ እሴት ተደርጎ ይቆጠራል።  የበዓሉ ተሳታፊዎች ክረምቱን አዝንቦ ምድሩን አረንጓዴ ላለበሰው፣ ወንዞችን በውሃ ለሞላው፣ ምንጮችን ላፈለቀው፣ ከብቶች እንዲረቡና እንዲፋፉ ላደረገው አምላክ /ዋቃ/ ምስጋና ያቀርባሉ። አሮጌው ዓመት አብቅቶ ለአዲሱ አቀባበል የሚደረግበት ዓመቱም የፍቅር፣ የሰላምና የብርሃን ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞት የሚገለጽበት የአዲስ ዓመት ብስራት ዕለት ተደርጎም ይወሰዳል ኢሬቻ። ይህን በዓል በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል /ዩኔስኮ/ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩም ይታወቃል። የዘንድሮውን በዓል ለማድመቅ ብሎም በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ለማገዝ ታስቦ የኢሬቻ ባዛርና ኤክስፖ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ኦሮሚያ ባህል ማዕከል ሲካሄድ ሰንብቷል። ላለፉት እየተካሄደ ነው። መስከረም 13 ቀን 2011 ዓ.ም በተከፈተውና ዛሬ ማምሻውን በሚጠናቀቀው ባዛር የተለያዩ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ ምግቦችና ኤሬቻን የሚያስተዋውቁ ስዕሎችና መጽሃፍት ቀርበዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎችና አቅራቢዎችም ባዛሩ የገበያ ትስስር ከመፍጠሩ ባሻገር ለኢሬቻ በዓል የሚቀርቡ የባህል ምግቦችና አልባሳትን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ይላሉ። ባዛሩን ለመጎብኘት የሚመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከማገናኘትና የባህል ትውውቅ ከመፍጠሩ ባሻገር ኢሬቻን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለኢሬቻ በአል ድምቀት የተለያዩ የኦሮሞ ባህልን ለማስተዋወቅ ትልቁ አቅም አለው የሚለው አቶ ፍሮምሳ ታደሰ ነው፡፡  ኢሬቻን በቢሾፍቱ ለመታደም ከሻሸመኔ የመጡትና ከባዛሩ አልባሳት ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ በላቸው ሹንቡራ አልባሳቱ የኦሮሞን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ብሄረሰብ ያማከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የባዛሩ መዘጋጀት ለበአሉ እውቅና ከመስጠት ባለፈ የብሄረሰቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ያጠናክራል ነው ያሉት።  የኢሬቻ ባዛርና ኤክስፖ አዘጋጅ ወይዘሮ መሰረት ጣባ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ሲካሄድ የመጀመሪያ የሆነው ባዛር በዓሉን ለማስተዋወቅና ባህሉን ለማሳደግ ጉልህ ሚና አለው ይላሉ። ስለ በአሉ የማያውቁ የተለያዩ ብሄረሰቦችና የውጭ አገር ዜጎች ኢሬቻን የሚተዋወቁበት እንደሆነም ተናግረዋል።  የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ.ም በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ይከበራል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም