የኢሬቻ በአል በሰላም እንዲከበር ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር ለመስራት ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በአል በሰላም እንዲከበር ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር ለመስራት ተዘጋጅተዋል
69
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 ነገ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ የሚከበረው የኢሬቻ በአል በሰላም ለማክበር የተመረጡ ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር ለመስራት መዘጋጀታቸው ተገለጸ። ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚመጡ የበአሉ ታዳሚዎች የበአሉን ባህላዊ እሴት መጠበቅ እንደሚገባቸውም የቱለማ አባገዳ አሳስበዋል። የፀጥታ ማስከበር ተግባሩን ከፖሊስ ጋር እንዲያከናውኑ 1 ሺህ 20 ወጣቶች (ፎሌዎች) ከመላው ኦሮሚያ ተመልምለው ተሰማርተዋል። የወጣቶቹ አስተባባሪ ወጣት ለማ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጸው ወጣቶቹ የፍተሻ፣ ቦታ የማስያዝና የመሳሰሉትን ስራዎች እንዲሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷቸዋል። ይህ የተደረገው ወጣቶቹ ከተለያዩ አካባቢዎች ከሚመጡ ቄሮዎች ጋር በስነ-ልቦና ስለሚቀራረቡ የሰላም ማስከበሩን ስራ ያቀለዋል በሚል እሳቤ ነው። ለክብረ በአሉ ወደ ቢሾፍቱ የሚመጡ ታዳሚዎች ለወጣቶቹ ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል። አዲሱ የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ በበኩላቸው ወጣቱ በአሉን ሲያከብር ለባህላዊ እሴቱ ተገዥ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል። ወጣቶች ከአለባበሳቸው ጀምሮ የሚያዜሟቸው ዘፈኖች ጭምር ከበአሉ አላማ ጋር የሚሄዱ መሆን አለባቸው ነው ያሉት። በአሉን ሲያከብሩ ከፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶች በጸዳ መልኩ በአንድነት ማክበር 'ይጠበቅባቸዋል' ሲሉም ተናግረዋል። በአሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በማድረግ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አባገዳው ጥሪ አስተላልፈዋል። በየአመቱ የሚከበረው ኢሬቻ የተጣሉ የሚታረቁበት ከመሆኑ ባሻገር ለአምላክ ምስጋና የሚቀርብበትም በአል ነው።