በስነ ጾታና ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለውን የክህሎት ከፍተት ለመሙላት ይሰራል

126
ሶዶ መስከረም 19/2011 በስነ ጾታና ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት እንደሚሰራ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ገለጸ፡፡ ኮሌጁ ከጀርመን ቻሪቲ ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በወጣቶች በስነ ጾታና ስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ያተኮረ ሴሚናር አካሂዷል ። በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቲችንግና ሪፈራል ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ባለሙያና የኮሌጁ ዲን ዶክተር ጌታሁን ሞላ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በስነ ጾታና ስነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ የባለሙያዎችን የዕውቀትና የክህሎት ክፍተት መሙላት ያስፈልጋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በባለሙያዎች ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት በቀጣይ ለመሙላት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል። መድረኩ የእዚህ አካል መሆኑን ገልጸው በእዚህም ከተለያዩ ዓለማት ከመጡ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ልምድንና ክህሎት መቅሰም አንደሚቻል አስረድተዋል። ከእዚህ በተጨማሪ መድረኩ በወጣቶች ስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማካሄድ እንደሚያግዝ ነው ያመለከቱት፡፡ ኮሌጁ በማህበረሰብ ጤና ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መርሃ ግብር  ከ80 በላይ ተማሪዎቸን በ2ኛ ድግሪ ደረጃ ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በኮሌጁ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ረዳት ፕሮፌሴር ወንድማገኝ ዻውሎስ በበኩላቸው መድረኩ በስነ ተዋልዶ ጤና ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መከላከል የሚያስችል ክህሎትን ለመቅሰም እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ እንደእርሳቸው ገለጻ በአካባቢውም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ የእናቶችንና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በተደረጉ ጥረቶች ለውጦች ቢኖሩም በሚፈለገው ልክ አይደለም። በመሆኑም ተዋልዶ ጤና የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ለህብረተሰቡ ውጤታማ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ወላይታ ሶዶ ወጣቶች የሚበዙበት አካባቢ ከመሆኑም በላይ ከስነ ተዋልዶ ዕውቀት ክፍተት የተነሳ እየተፈጠረ ያለውን ጫና ለመቀነስ ሲባል መድረኩ መዘጋጀቱን የገለጹት  ደግሞ በኮሌጁ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያ አቶ ፈቃዱ ኤልያስ ናቸዉ፡፡ ከጀርመን ቻሪቲ ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት የመጡት ሚስ አንድሪያ ስታንግሊማይር በመድረኩ ላይ "የስነ ተዋልዶ ጤና ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃና ተግዳሮቶች" በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። የስነ ተዋልዶ ጤና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠውን ትኩረት ያህል ውጤታማ አለመሆኑንና በተለይ በአፍሪካ ተመሳሳይ ደረጃ ባላቸው አገራት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በግልጽ ያለመነጋገር፣ በቅንጅትና በትኩረት ያለመስራት፣ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ዕውቀትና ክህሎት በየወቅቱ በጥናት ለይቶ ያለማሳደግና ሌሎችም ችግሮች በዘርፉ ላይ እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡ የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው በትምህርትና በሌሎች ቁሳቁሶች ከመደገፍ አንጻር ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡ ወጣቱ በነገዋ ኢትዮጵያ ላይ ሚናውን በአግባቡ እንዲጫወት ከተፈለገ በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት ስጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ሚስ አንድሪያ አሳስበዋል፡፡ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው በእዚህ መድረክ ከስነ ጾታና ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ ልምዶችና ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በመድረኩ  ከ13 ሃገራት በላይ የመጡ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም