አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በበጋ ወቅት እርጥበታማ የአየር ጠባይ ይኖራቸዋል....የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ

84
አዳማ 19/1/2011 በመጪው የበጋ ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል እርጥበታማ የአየር ጠባይ እንደሚኖራቸው የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው የክረምት ወቅት የአየር ፀባይ ግምገማና የመጪው በጋ ወራት ትንበያን አስመልክቶ ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል ። በዚህ ወቅት የኤጀንሲው የአግሮ ሚቲዎሮሎጂ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ይመር አሰፋ እንዳስታወቁት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆነው የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች በአብዛኛው ከመደበኛው በላይ ዝናብ ያገኛሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ የአየር ጠባይ ክስተትን ግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ወቅት የሚያከናውነውን የግብርና ሥራና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል። በተለይ አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ በወቅቱ የሚገኘውን እርጥበት ለግብርና ስራው በአግባቡ እንዲጠቀምበት አቶ ይመር አስገንዝበዋል። በአንጻሩ በበጋ ወቅት ደረቅ ሆነው የሚቆዩት የሀገሪቱ ሰሜናዊ አጋማሽ ክፍሎች ወቅታዊ ያልሆነ ዝናብ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስታውቀዋል። የምክክር መድረኩን የመሩት የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው ኤጀንሲው በዘርፉ አሉ የሚባሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችና ግበዓቶችን በመጠቀም የአየር ሁኔታና ጠባይ ትንበያ መረጃዎችን በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል። በዘንድሮው የክረምት ወቅት ብቻ ኤጀንሲው የሰጠውን ትንበያና በተጨባጭ የነበረውን የአየር ሁኔታ ሲገመገም ከሞላ ጎደል የተጣጣመ እንደነበር አስረድተዋል ። ይህም ለኢኮኖሚው በተለይም ለግብርና ዘርፍ አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት የኤጀንሲውን መረጃዎች በይበልጥ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል። "ኤጀንሲው በሚሰጠው አገልግሎት የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለማርካትና በተጠቃሚዎች ዘንድም የባለቤትነት ስሜት ለመፍጠር በየጊዜው የውይይት መድረክ በመፍጠር ከዕቅድ ጀምሮ እስከአፈጻጸሙ  ግብረ መልስ ያሰባስባል" ብለዋል። ይህ መድረክም የእዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት። በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው በዚሁ መድረክ ላይ ከክልልና ከፌዴራል የተውጣጡ የኤጀንሲው አገልግሎት ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም